“ፍፁም ለግብ የቀረቡ ኳሶችን የመፍጠር አቅማችን ደካማ ነው” አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው
“አንዳንዴ እንደዚህ ይሆናል ብትጫወትም ዕድለኝነትን ይፈልጋል” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ
የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ መካከል ተከናውኖ ያለ ጎል ከተቋጨ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አሰልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሲዳማ ቡና
በመከላከሉ ጠንካራ ሆነው አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ስለወጡበት ጨዋታ…
“ልክ ነህ ዒላማውን የጠበቀ የሚባለው በግብ መሃከል ሲሆን ነው ኢላማውን ጠበቀ የሚባለው ወይም ግብ ጠባቂ ሲያድን ፣ አለዚያ የግቡ ቋሚ እና አግዳሚ ሲመልሰው ነው። ከዛ ውጪ ብዙም ሳይርቁ የሚደረጉ ሙከራዎች ነበሩ ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ግን ፍፁም ለግብ የቀረቡ ኳሶችን የመፍጠር አቅማችን ደካማ ነው ፣ ይሄ ደግሞ መስተካከል ያለበት ነው ያው ግልፅ ስለሆነ ማለት ነው። የእነዚህ ፍፁም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች መፍጠርም ያስፈልጋል። ምናልባት ሁለተኛው አጋማሽ የበለጠ በከፍተኛ ሁኔታ ተጭነን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። በዕርግጥ እነርሱ በመልሶ ማጥቃት ለመምጣት ሞክረዋል ቢሆንም ፍፁም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን መፍጠር ውስንነት አለብን የሚስተካከል ነው።”
ከኢትዮጵያ መድኑ አንፃር በዛሬው ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ስለማድረጋቸው …
“የቀየርነው ሁለት ተጫዋች ነው ይሄ ደግሞ የሚያጋጥም ነው ፣ የታክቲካል ለውጥ ይኖራል ምንአልባት ዛሬ የተጫወትነው በ4-5-1 የጨዋታ ሲስተም ነው መስመር ላይ ሙሉቀንን አስገብተን ሀብታሙን አሳርፈናል ፣ ከፊት ላይ ማይክልን አወጣን ቡልቻን ከፊት እንዲጫወት አደርግነው ይሄን ነው ያደረግነው። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ገብተዋል እነዚህ ተጫዋቾች ያን ያክል የጎላ ልዩነት የለም መነሻችን ከሳምንቱ ጨዋታ በኋላ የነበሩንን ልምምዶች እና የዛሬው ተጋጣሚያችንን ታሳቢ ያደረገ ነው።”
እንደ አጠቃላይ ቡድኑን ከያዙ በኋላ ስለነበሩት ሁለቱ ጨዋታዎች…
“እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነው ፣ ምንድነው ጥሩ የሚያሰኘው በሁለት ጨዋታ በ180 ደቂቃ ውስጥ ምንም ኳስ አልተቆጠረብንም ፣ በአንፃሩ ያገባነው አንድ ነው ፣ በመከላከሉ ጥሩ ነው ፣ የማጥቃት ሀይላችን ደግሞ ውስንነት እንዳለብን ማሳያ ነው። ስለዚህ የመከላከል አቅማችንን አሁንም እያጠናከርን ፣ የማግባት አጋጣሚያችንን ወደ ፊት ከፍ ማድረግ አለብን ፣ ካላስቆጠርን ምንም ላይጠቅም ይችላል።”
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለው ግብ ሳያስቆጥሩ ያለ ጎል ስላጠናቀቁት ጨዋታ…
“ከባለፈው ጨዋታ የዛሬው የተሻለ ነው። በኳስ ቁጥጥር የተሻልን ነበርን ብዬ ባስብም ሁሌም የኳስ ቁጥጥር ቢኖርም ከጎል ጋር የታገዘ ቢሆን ውጤታማ ትሆናለህ። ዛሬ ቡድኔ መጥፎ አይደለም።”
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት አቻ ሁለት ሽንፈት ስለመኖሩ እና ቡድኑ ስለጎደለው ነገር….
“ከጉዳት ተያይዞ ነው ፣ የተወሰኑ ተጫዋቾች ጉዳት አለባቸው ፣ ሁለተኛ ደግሞ እንደዚህ አይነት ነገሮችም ይከሰታሉ እንደ አጀማመራችን መሄድ ያለብንን ደረጃ አልሄድንም ያም ቢሆን ግን እጅግ መጥፎ አይደለም መሻሻሎች አሉ በጎል ይታጀባል ፣ የተሻለ ደረጃ ይኖረናል።”
የግብ ዕድል የመፍጠር ችግር ከአማካይ የፈጠራ ማነስ የተነሳ ወይስ የአጥቂዎቹ የጥምረት ክፍተት…
“መስዑድን እና ሀይደርን ይዘህ ወይም አጠገባቸው ያለውን አቡበከርን ይዘህ ፈጣሪ ተጫዋች አጥቻለሁ ማለት ከባድ ነው ፣ እነዚህ በጣም ፈጣሪ ተጫዋቾች ናቸው። ብዙ ጊዜ ያባከነው ፖሴሽን እግር ኳስ ላይ ነው እና እርሱን እየተጫወትን ከጎላችን ቶሎ የምንወጣበት ነው ቢሆንም ግን ደርሰናል ፣ የአማካዮቹ ችግር ነው ብዬ አላስብም። አንዳንዴ እንደዚህ ይሆናል ብትጫወትም ዕድለኝነትን ይፈልጋል እኔ ቡድኔ ላይ መሻሻል ነው እያየው ያልሁት።”