ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ የመጀመሪያ ሽንፈቱን በወላይታ ድቻ ካስተናገደ በኋላ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የድኅረ ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈት ስላስተናገዱበት ጨዋታ…
“ጨዋታው ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ጥሩ ፉክክር ፣ ለተመልካችም ሳቢ ነበር ብዬ አስባለሁ። ያሰብነውን ምናልባት በመጨረስ ረገድ ጎል ካለ ማግባታችን በቀር ግልፅ የሆኑ የግብ ዕድሎችን ከእነርሱ በተሻለ ፈጥረን ነበር። በረኛው ያወጣቸው ኳሶች አንድ አራት የሚሆኑ በተለይ ግልፅ የሆኑ በጣምም ግልፅ የሆኑ መግባት ቢችሉ ኖሮ ውጤቱ እንደዚህ ላይሆን ይችል ነበር። በተረፈ ጨዋታው በጣም ፈጣን ፣ ሽግግሮችም የነበሩት እና ጥሩ ፉክክርም የታየበት ነው ብዬ አስባለሁ።”
ተጋጣሚያችሁን በጠበቃችሁት ልክ አግኝታችሁታል ማለት ይቻላል…
“ድቻ ከዚህ በፊትም እንደምናውቀው ጠንካራ ከምንላቸው ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። በተለይ በመልሶ ማጥቃት ፣ የቆሙ ኳሶች ላይ ደግሞ ተነሳሽነታቸው እንደገና ደግሞ ኳስም የሚጫወት ቡድን ነው ፣ ምናልባት ከዚህ የተሻለ ውጤት ይኖረው ነበር ነገር ግን ወጣ ገባ ባሕሪው አንድ ጊዜ እላይ ይወጣል አንድ ጊዜ ደግሞ ይወርዳል ከዛ በስተቀር ድቻ ሊጉ ላይ ከምርጥ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። ባገኘነው የጨዋታ አቀራረብ ነው የቀረቡት ጥሩ ነው በኳስ ቁጥጥርም የተሻልን ነበርን ብዬ አስባለሁ በተለይ የእነርሱን መልሶ ማጥቃት ለማቆም ብዙ አልተቸገርንም መልሶ ማጥቃታቸው በጣም ጠንካራ እንደሆነ ይታወቃል። በጣም ደካማ ፓርታችን የነበረው የፈጠርናቸውን የግብ ዕድሎች እነርሱን አለመጠቀማችን ደካማ ጎናችን ነበር ብዬ አስባለሁ።”
አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ
ጥሩ ፉክክር ከነበረው ጨዋታ አሸንፈው መውጣታቸው…
“እጅግ በጣም ጥሩ ነው ፣ ማራኪ የሆነ እግር ኳስ ተጫውተን ወጥተናል። ተፎካካሪያችንም እጅግ በጣም ጠንካራ ነው፣ ሊጉን እየመራ ያለ ቡድን ነው አንድ ለባዶ አሸንፈናል።”
አዛሪያስ አቤል በሁለተኛ ጨዋታው ጎል ማስቆጠሩ እና በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀሱ…
“አዛሪያስ በጣም ትልቅ ተጫዋች ነው ፣ ወደፊት ትልቅ ቦታ መድረስ የሚችል ጥሩ አቅም ያለው ልጅ ነው። በቀጣይ ዓመታት ውስጥ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ከምናያቸው ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።”
የቡድኑ ጠንካራ ጎን…
“ሕብረታችን ትልቁ ጥንካሬያችን ነው። ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው ተነሳሽነት አለ ፣ ፍላጎታቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ተጫዋቾቻችን ከምንም በላይ ደግሞ ሕብረታችን ነው። የትኛውም ተጫዋች በየትኛውም ደቂቃ ተቀይሮ ቢገባ በገባበት ሰዓት ዋጋ ከፍሎ ይወጣል ለቡድኑ።”
ወሳኙ አማካይ አብነት ደምሴ በጉዳት መውጣቱ እና ስለ ጉዳቱ ሁኔታ…
“ብዙ የከፋ አይደለም ፣ ለሚቀጥለው ጨዋታ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ ግን እሱ ባይኖርም የእርሱን ቦታ ተክተው መጫወት የሚችሉ ሌሎች አማራጮች አሉን ያን ያህል የሚያሰጋን አይደለም።”