የፕሪሚየር ሊጉ አወዳዳሪ አካል ትናንት የተጠናቀቀውን የጨዋታ ሳምንት ተንተርሶ ቅጣቶችን ሲያስተላልፍ ወልቂጤ ከተማ የሳምንቱ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት መርሀግብር ከተጠናቀቀ በኋላ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ከዳኞች እና ታዛቢዎች ያገኘውን ሪፖርት ተንተርሶ ኮሚቴው የቅጣት ውሳኔዎችን በክለቦች እና በተጫዋቾች ላይ አሳልፏል።
ወልቂጤ ከተማ በፋሲል ከነማ 1-0 ሲረታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኛ ላይ አፀያፊ ስድብን ስለ መሰንዘራቸው በሪፖርት በመገለፁ በክለቡ ላይ የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልበት በተጫዋች ደረጃ ደግሞ የሀምበርቾ ከባህር ዳር ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቀበት ጨዋታ በ38ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደው አማካዩ ብረክ ቃልቦሬ በጨዋታው የዕለቱ ዳኛ ላይ አፀያፊ ስድብን በመሰንዘሩ የሦስት ጨዋታ እና የ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ክፍያን እንዲከፍል ተወስኗል። በተመሳሳይ የሀምበርቾ ተጫዋቾች በባህር ዳሩ ጨዋታ አምስት ቢጫ በመመልከታቸው ቡድኑ ላይ የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል።