በምድብ “ለ” የ12ኛ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ወሎ ኮምቦልቻ እና ደብረብርሃን ከተማ ድል ሲያደርጉ ደሴ ከተማ ነጥብ ተጋርቷል።
ረፋድ አራት ሰዓት ሲል የተጀመረው መርሃ ግብር ጠንካራውን ኦሜድላ በምድቡ ግርጌ ላይ የሚገኙትን ወሎ ኮምቦልቻን ያስተናገዱበት ነበር።
ጥሩ ፉክክርን በተመለከትንበት በዚህ ግጥሚያ ሁለቱም ቡድኖች ደረጃቸውን ለማሻሻል በአዎንታዊ ባደረጉት ጨዋታ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተን ነበር።
ከብዙ የግብ ሙከራዎች በኋላ ጥረታቸው የሰመረው ኦሜድላዎች በ33ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ቶማስ ላይ የወሎ ኮምቦልቻ ተከላካዮች በሰሩበት ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ ኤፍሬም በመምታት ኳስና መረብ አገናኝቶ ኦሜድላዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ወሳኙን ነጥብ ለማስመዝገብ በተለይም ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጠንከር ብለው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወሎ ኮምቦልቻዎች የተሻለ የሚባልን ጥረት ሲያደርጉ አስውለናል።
የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ ሰከንዶች አስቀድሞ ዮሐንስ ኪሮስ በራሱ ጥረት ከርቀት አክርሮ በመምታት ያስቆጠራት ግብ ሁለቱ ቡድኖች በአቻ ውጤት ወደ እረፍት እንዲያመሩ ያስገደደች ነበረች።
ሁለቱም ቡድኖች በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቃዛ የጨዋታ እንቅሰቃሴን አስመልክተዋል።ሆኖም ግን ወሎ ኮምቦልቻዎች ወሳኙን ነጥብ ለማሳካት በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራ ረገድ ከተቃራኒ ቡድን አንፃር በመጠኑ ተሽለው የገቡበት አጋማሽ ነበር።በ52ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግብ አስቆጣሪው ዩሐንስ ኪሮስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ወሎ ኮምቦልቻዎች መሪነት ወደ ሁለት በማሳደግ ጨዋታው በወሎ ኮምቦልቻዎች 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቀን ስምንት ሰዓት ላይ የጀመረው ሁለተኛው ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማን ከደሴ ከተማ አገናኝቷል።በመጀመሪያው አጋማሽ ቢሾፍቱ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር ሆነ በግብ ሙከራዎች ረገድ ብልጫ የወሰዱበት ነበር።
ይህ ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቶ ግቦችን አከታትለው ማስቆጠር ችለዋል።በ30ኛው ደቂቃ አብዱልዓዚዝ ዑመር ከዳዊት ሽፈራው ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ይዘው የገቡትን ኳስ አብዱልዓዚዝ ሲያስቆጥር በደቂቃዎች ልዮነት ደግሞ በተመሳሳይ ራሱ አብዱልዓዚዝ ዑመር በደሴ ከተማ ተጫዋቾች ስህተት ታግዞ ያገኘውን ኳስ በማስቆጠር ቡድን 2-0 መሪ ማድረግ ችሏል።
ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ቢሾፍቱዎች በ40ኛው ደቂቃ ዳዊት ሽፈራው ላይ ጥፋት በመሰራቱ የተገኘውን የቅጣት ምት ኳስ ራሱ ደዊት ሽፈራው በድንቅ ሁኔታ በመምታት አስቆጥሮ አጋማሹ በቢሾፍቱዎች 3-0 መሪነት እንዲቆጭ አስችሏል።
ፍፁም ደካማ አጋማሽ ያሳለፉት ደሴ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የተሻለ እንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል።ከብዙ የግብ ሙከራዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው ሙሉጌታ ከፀጋ ደርቤ የተሻገረለትን ኳስ በማስቆጠር የግብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል።
ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥሩ የነበሩት ደሴ ከተማዎች ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር ሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው።ግብ ያስተናገዱት ቢሾፍቱዎች በተዘናጉበት ቅፅበት በ77ኛው ደቂቃ አምበላቸው ሚካኤል ለማ ከብሩክ ታምሩ ጋር ተቀባብሎ ኳስና መረብ ያገናኘ ሲሆን በዚህ ያላበቁት ደሴዎች በተጨማሪ ደቂቃ አቡሽ ደርቤ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ታፈሰ ሰርካ ኳስና መረብን አገናኝቶ ሁለቱ ቡድኖች 3ለ3 በሆነ ውጤት ነጥብ እንዲጋሩ አስችሏል።
ስምንት ግቦች የተስተናገዱበት የዕለቱ የመጨረሻ መርሃግብር የካ ክ/ከተማን ከደብረብርሃን ከተማ አገናኝቶ በደብረብርሃን አሸናፊነት ተጠናቋል።
በመጀመሪያ አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብለጫ የወሰዱት የካ ክፍለ ከተማዎች በ29ኛው ደቂቃ ደረጀ ነጋሽ በግል ጥረት ኳስን ይዞ በመግባት ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚ አድርጓቸዋል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ደብረብርሃኖች በ33ኛው ደቂቃ የሰሩትን ሰህተት በመጠቀም ብስራት ታምሩ ኳስና መረብ በማገኘናኘት የየካን መሪነት ወደ ሁለት ቢያሳድግም ደብረብርሃኖች በመልሶ ማጥቃት ሄኖክ አየለ ባስቆጠራት ግብ የግብ ልዮነታቸውን ወደ አንድ አጥብበው ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
ከመጀመሪያው አንፃር የተሻለ የሜዳ ላይ ፉክክር በተመለከትንብ በሁለተኛው አጋማሽ በ57ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ ፍለጋ ይታትሩ የነበሩት የደብረብርሃን ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ጥሩ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ሄኖክ አየለ አስቆጥሮ ቡድኖቹን አቻ አድርጓል።
ሆኖም ግን ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት የዘለቀው ለሶስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር ፤ በ60ኛው ደቂቃ ክብሮም ፃድቅ በራሱ ጥረት ከርቀት ባስቆጠራት ግብ የካዎችን ዳግም መሪ ሲያደርግ በ72ኛው ደቂቃ ሄኖክ አየለ በየካ ክ/ከተማ ተጫዋቾች ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ሐት-ትሪክ በሰራበት ግብ የጨዋታውን ውጤት ወደ ሶስት አቻ መቀየር ችሏል።
እጅግ አስደናቂ አጨራረስ በነበረው በዚሁ ጨዋታ ደብረብርሃን ከተማዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በነበሩት ሶስት ተጨማሪ ደቂቃዎች በሄኖክ አየለ እና በሃይሉ ተሻገር አማካኝነት ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ሙሉ ሶስት ነጥቡን ይዘው መውጣት ችለዋል።