የአስራ አንደኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይጀምራሉ፤ የሳምንቱ መክፈቻ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል
ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ነጥብ ከመጋራት የመጡትን ኢትዮጵያ ቡናዎችን ከሀዲያ ሆሳዕና የሚያገናኘው ጨዋታ የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር ሆኗል።
ከሰርቢያዊው አሰልጣኝ ኒኮላ ኮቫዞቪች ጋር ውል ያቋረጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመንበሩ ወጣቱ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ከተቀመጠ በኃላ ባደረጓቸው የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ተከታታይ ድሎችን ቢያስመዘግቡም ባለፈው ሳምንት ግን ባልተጠበቀ መልኩ በሻሸመኔ ከተማ ለመሸነፍ ተቃርበው በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
አሁን ላይ በ15 ነጥቦች በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው በተለይ ወደ ራሱ ሳጥን ተጠግቶ ከሚከላከል ተጋጣሚ ጋር በትዕግሥት በመንቀሳቀስ የግብ እድሎችን ከመፍጠር አንፃር ያለበትን ውስንነት በድጋሚ የተመለከትን ሲሆን በነገው ጨዋታ ከዚህ አንፃር ሀዲያዎች ከኳስ ውጭ ካላቸው ጠንካራ አወቃቀር አንፃር የማጥቃት ጨዋታቸውን ከዚህ ሁኔታ አንፃር በደንብ ሊቃኙ ይገባል።
እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ዋና አሰልጣኛቸውን አሰናብተው ምክትላቸውን በጊዜያዊነት ወደ ዋና አሰልጣኝነት ያመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎችም ከአስቀያሚው አጀማመራቸው ማግስት ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማን በማሸነፍ ከድል የታረቁ ቢመስልም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብን በመጋራት ነጥባቸውን ወደ 12 በማሳደግ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱን የመዲይቱን ክለቦች በተከታታይ የሚገጥሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነገም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ጥበቅ ያለ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ሲጠበቅ በአንፃሩ ግን የሚያገኟቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በመጠቀም ረገድ ግን አፈፃፀማቸውን ማሻሻል ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ወሳኙ አማካያቸው አማኑኤል ዮሀንስን በጉዳት ሲያጡ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅም በግል ጉዳይ ምክንያት ለዚህ ጨዋታ አይደርስም።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል በአባቱ ሞት ምክንያት ከቡድኑ ጋር የሌለው ዳዋ ሆቴሳ በነገው ጨዋታ ተሳትፎ አይኖረው። ሔኖክ አርፊጮ ፣ ብሩክ ማርቆስ እና ካሌብ በየነም በጉዳት አይኖሩም።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በዋናነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት ተካልኝ ለማ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።
ባህርዳር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በተመሳሳይ የባዶ ለባዶ ውጤት ያስመዘገቡት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ የጣሉት ባህርዳር ከተማዎች በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የጣና ሞገዶቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተመሳሳይ የሚባል ፈተና ገጥሟቸዋል፤ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ ወደ ራሳቸው ግብ ክልል በጥልቀት ተመልሰው የሚከላከሉ ቡድኖች የገጠሙው ባህርዳሮች በሁለቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የተጋጣሚያቸው የተከላካይ ክፍል ሰብረው በርካታ ዕድሎች መፍጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግብ ማስቆጠር ያልቻለውን አጨዋወት ላይ ውስን ለውጥ የሚያደርጉበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ በነገው ዕለትም በተመሳሳይ አዲስ አሰልጣኝ ከቀጠረ በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግብ ያላስተናገደው ሲዳማ ቡናን እንደመግጠሙ በሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ ላላቸው ውስንነት መፍትሔ ማበጅት ይጠበቅባቸዋል።
የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች መሰብሰብ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በአስራ ሁለት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከዚህ ቀደምም ጥሩ የነበረውን የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ማስቀጠል ችለዋል፤ ባደረጓቸው በሁለት ጨዋታዎችም ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አላቸው። ሆኖም ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ያለውን ውስንነት መቅረፍ አልቻሉም፤ ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረጉት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ወጥተዋል። የቡድኑ የማጥቃት እጨዋወት የማስተካከል ስራም የአሰልጣኝ ዘላለም ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
ባህርዳር ከተማዎች ከአደም አባስ ውጭ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በአንፃሩ ባለፈው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ያልተሰለፈው ፍሬዘር ካሳ ለጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። ሲዳማ ቡናዎችም በኩልም በተመሳሳይ በጉዳትም ሆነ ቅጣት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች የለም።
የዚህን የምሽት መርሀግብር ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሻረው ጌታቸው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ ሆኗል።