በምሽቱ መርሐግብር ሲዳማ ቡና ባህር ዳር ከተማን 2ለ0 መርታት ችሏል።
በምሽቱ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና ሲገናኙ ባህር ዳር ከሀምበርቾ ጋር ባለፈው ጨዋታ ነጥብ ከተጋራበት ስብስቡ በመሳይ አገኘሁ ምትክ ረጀብ ሚፍታህን ሲያስገባ ሲዳማ ቡና ከአዳማው ጨዋታ አንፃር የአራት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። ብርሀኑ በቀለ ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና ቡልቻ ሹራ ወጥተው ደስታ ዮሐንስ ፣ አቤኔዘር አስፋው ፣ እንዳለ ከበደ እና ዳመነ ደምሴ በምትኩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
12 ሰዓት ላይ በኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ባህር ዳሮች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ችለው 4ኛው ደቂቃ ላይም የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ አለልኝ አዘነ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ በደካማ አጠባበቅ እንደምንም ወደ ውጪ አስወጥቶታል።
ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ሲዳማዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ደስታ ዮሐንስ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ ጊት ጋትኩት በግንባር በመግጨት አስቆጥሮታል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ 13ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ፍጹም ጥላሁን ከሀብታሙ ታደሰ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።
18ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኙን የመሃል ተከላካያቸውን ደስታ ደሙን በጉዳት አጥተው በደግፌ ዓለሙ የተኩት ሲዳማዎች 30ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ያሬድ ባዬህ ዳመነ ደምሴ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ደስታ ዮሐንስ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል።
በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ቅብብሎች እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ባህር ዳሮች 35ኛው ደቂቃ ላይም ከቅጣት ምት ፍራኦል መንግሥቱ ባሻገረው እና አለልኝ አዘነ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል በወጣበት ኳስም ሙከራ ማድረግ ሲችሉ 44ኛው ደቂቃ ላይ ግን ወሳኙን የመሃል ተከላካያቸውን ያሬድ ባየህን በሁለት ቢጫ ካርድ አጥተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ባህር ዳር ከተማዎች ፍሬዘር ካሳን በረጀብ ሚፍታህ ቀይረው በማስገባት እና የኋላ መስመራቸውን በማደላደል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ሲዳማዎች በአንጻሩ ውጤቱን ለማስጠበቅ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲጥሩ ተስተውሏል።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ባህር ዳሮች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራቸውን 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ፍጹም ጥላሁን ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ይዞበታል።
ጨዋታው 81ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሲዳማዎች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ከመሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ሾልኮ በመውጣት ማስቆጠር ችሏል። በጣና ሞገዶቹ በኩልም በመጨረሻው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበት ጨዋታው በሲዳማ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።