ለረጅም ወራት በጉዳት ከሜዳ ርቆ ትናንት ወደ ጨዋታ ከተመለሰው የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተጫዋች ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።
በ2015 የውድድር ዓመት የሊጉ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲከናወኑ ጥቅምት 25 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ጋር እያደረገ በነበረው ጨዋታ የቡድኑ የመስመር ተከላካይ አሥራት ቱንጆ 70ኛው ደቂቃ ላይ በገጠመው ጉዳት ከሜዳ ለመውጣት መገደዱ ይታወሳል። ከዚህ ቅፅበት ጀምሮ በዋልያዎቹ እና በክለቡ በወጥነት ሲያገለግል የምንመለከተው ተጫዋች ወደ ሜዳ ሳይመለስ ቀርቷል። ይህንን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በላይ በህክምና እና በማገገሚያ ሥራዎች ላይ የቆየው አሥራት ትናንት ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባደረገው ጨዋታ ዳግም ወደ እግርኳስ ተመልሶ ለ75 ደቂቃዎች ተጫውቶ መውጣት ችሏል። ይህንንም አስመልክቶ ሶከር ኢትዮጵያ ከተጨዋቹ ጋር ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጋለች።
“የጉልበት ጉዳት ነበር ያጋጠመኝ ፤ ACL ነበር የጉዳቱ ዓይነት። ለዚህም ቀዶ ጥገና አደረኩኝ። በመቀጠል ፊዚዮቴራፒ ነው ለረጅም ጊዜ የተከታተልኩት። ከዚያ የተለያዩ የማጠንከሪያ ሥራዎች በመስራት እግሬን ማጠንከር ችያለሁ። በፊዚዮቴራፒስቷ በኩል ነበር ፤ የማደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በየጊዜው ለውጡንና ያለውን መረጃ እነግራታለሁ። የሚሰማኝ ስሜት ካለም አወራታለሁ። ጥሩ ነበር ፤ ትንሽ የተወሰነ ህመም ነበረው። በሂደት እየጠፋ እየጠፋ የጥንካሬ ሥራዎችን እየሰራሁ ወደ ሜዳ ተመልሻለሁ።”
የጉዳቱ ክብደት በሥነልቦናው ረገድ ስለፈጠረበት ጫና…
“በፊትም ስፖርቱ ላይ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ ፤ በሀገራችን ደረጃ ትንሽ የሚያስቸግር ነበር። አሁን ላይ ግን እኔ ከመሰራቴ በፊት ተሰርተው የተመለሱ ልጆች ነበሩ። እነሱ የተወሰነ በራስ መተማመን ጨምረውልኛል። በተጨማሪም በውጪው ዓለምም ብዙ ተጫዋቾች እየተጎዱ እንደሚመለሱ አየሁኝ። በመሆኑም የመመለስ ዕድሌ ሰፊ መሆኑን እርግጠኛ ነበርኩ። ዶክተሩንም ሳወራው ካለ ነው ህመሙ ከሌለ 85 ፐርሰንት የሚያግዝህን ነገር ነው የሚጨምርልህ እና እርግጠኛ ነበርኩኝ ፤ አልተጠራጠርኩም።”
ወደ ሜዳ መመለሱ ስለፈጠረበት ስሜት…
“በጣም ነበር ደስ ያለኝ። በህክምናው እርግጠኛ ብሆንም ዳግም ወደ ሜዳ በመመለሴ አምላኬን በጣም አመሰግነዋለው። በጣም ነበር ደስ ያለኝ።”
ወደቀድሞው አቋሙ ስለመመለስ ህልሙ…
“ወደ ቀደመው አቋሜ ለመመለስ ጠንክሮ መስራት ነው። ጠንክሬ ሰርቼ ቶሎ እመለሳለሁ ብዬ ነው የማስበው።”