የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአስራ አንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲካሄዱ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ መቻል
የአሸናፊነት መንገዳቸውን ለማስቀጠል አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡትን ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።
ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ኢትዮጵያ መድንን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት ብርቱካናማዎቹ ነጥባቸውን አስራ አንድ ማድረስ ችለዋል። ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች አስተናግደው ነበር። ከመድን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ግን ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በመከላከሉ ረገድ መጠነኛ መሻሻሎች አድርገዋል። በማጥቃቱ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ቡድን ያሳዩን አሰልጣኝ አስራት አባተ ከዚህ በፊት የታዩባቸውን የመከላከል ችግሮች በውስን መልኩ ቀርፈው መቅረባቸው ቡድኑን አሻሽሎታል። በነገው ጨዋታም የመከላከል ክፍሉን ጥንካሬ ከማስቀጠል አልፈው በውድድር ዓመቱ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ይዞ ለቀረበው መቻል ሊፈትን የሚችል የማጥቃት አጨዋወት ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ የወጣው ቻርለስ ሙሴጌ ለዚ ጨዋታ ብቁ መሆኑም ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። አሰልጣኝ አስራት አባተ በተመስገን ደረሰ ፣ ቻርለስ ሙሴጌ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ኤፍሬም አሻሞ መጠነኛ ጉዳቶች ምክንያት የሳሳውን የፊት መስመራቸው ክፍተት ለመድፈን የሄዱበት መንገድ በጥሩ ጎኑ ይነሳል።
በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙት መቻሎች ከመሪው ንግድ ባንክ እኩል ሀያ ሦስት ነጥብ ሰብስበው በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል። በነገው ዕለትም ሊጉን ለመምራት ወይም ልዩነቱን አስጠብቆ ለመጓዝ ከብርቱካናማዎቹ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። መቻሎች በውጤት ረገድ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ቢገኙም ቡድኑ እንዳለው የስብስብ ጥራት የሚመጥን እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከእንቅስቃሰው ይልቅ ለውጤቱ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የገለጹት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ገንብተው ቡድኑ ተፎካካሪ ማድረግ ቢችሉም ጨዋታ በመቆጣጠር ረገድ ያላቸውን ክፍተት ግን ይበልጥ ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ከቅዱስ ጊዮርጊስና ሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ጨምሮ በበርካታ አጋጣሚዎች ላይ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የሚታይባቸውን መቀዛቀዝ ለመፍታት ጨዋታ የሚቆጣጠሩበት የተሻለ መንገድ ማበጀት ይኖርባቸዋል። ለኳስ ቁጥጥር አመቺ የሆነው የተከላካይና የአማካይ ክፍሉም በተሻለ ትዕግስት ኳሶችን በማንሸራሸር የጨዋታውን ግለት መቆጣጠር ይጠበቅበታል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተመስገን ደረሰ ፣
አብዱልፈታህ ፣ ያሲን ጀማልና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም ፤ ከዚ በተጨማሪ ዳዊት እስጢፋኖስ በቤተሰብ ችግር ምክንያት በነገው ጨዋታ ተሳትፎ አይኖረውም። ሆኖም ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ቻርለስ ሙሴጌ ለነገው ጨዋታ ብቁ ነው። በመቻል በኩልም በልምምድ ጉዳት ካስተናገደው ተስፋዬ አለባቸው ውጭ ስብስቡ ሙሉ ነው።
በዋና ዳኝነት ተካልኝ ለማ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሻረው ጌታቸው በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ መድን
ከሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገቡ ሁለት ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከተከታታይ ሽንፈት አልባ ጉዞ በኋላ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ያስተናገዱት የሊጉ መሪ ንግድ ባንኮች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ። ንግድ ባንኮች በመጨረሻው ጨዋታ በብዙ መለኪያዎች ወርደው ታይተዋል። በተለይም ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው የቡድኑ የፊት መስመር መጠነኛ መቀዛቀዞች ታይቶበታል። ቡድኑ ምንም እንኳ ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም በጥራትም ሆነ በቁጥር ረገድ ግን ከባለፉት ሳምንታት የወረደ ነበር ማለት ይቻላል። ከሊጉ በብዙ ረገድ የተሻለና ወጥነት ያለው ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ የወላይታ ድቻን አስፈሪ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት መመከት የቻለ አደረጃጀት ይዘው ቢገቡም በማጥቃቱ በኩል ግን መሻሻል የሚገባው የአፈፃፀም ችግሮች ነበሩባቸው። በነገው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ትልቅ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም በመጨረሻው ጨዋታ በፊት መስመሩ የተስተዋለን ክፍተት ቀርፈው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ኢትዮጵያ መድኖች በዘጠኝ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። መድኖች ምንም እንኳ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ቢያስተናግዱም ሽንፈት ካስተናገዱባቸው ሌሎች ጨዋታዎች በአንጻራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በጨዋታው የፈጠሯቸው የግብ ዕድሎችና የነበራቸው የተሻሻለ የጨዋታ ፍላጎትም የዚ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታም የሊጉን መሪ እና በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደ መግጠማቸው በብዙ መልኩ ተሻሽለው መቅረብ ይገባቸዋል። አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በቅድሚያ ባለፉት ጨዋታዎች የትኩረት ማጣት ችግር የተስተዋለበት የተከላካይ ክፍላቸው ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ተጋጣሚያቸው በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.6 ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የፊት መስመር ያለው ቡድን እንደመሆኑ በመከላከሉ ረገድ ልዩ ዝግጅት አድርገው መግባት ቀዳሚ ሥራቸው መሆን አለበት። ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገው የፊት መስመራቸው ስልነት ከፍ ማድረግ ሌላው የቤት ሥራቸው ነው።
በንግድ ባንክ በኩል ብሩክ እንዳለ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። ገናናው ረጋሳ ደግሞ ከጉዳቱ በማገገም ለጨዋታው ዝግጁ ቢሆንም ለመጫወት የአሰልጣኙን ውሳኔ የሚጠብቅ ይሆናል። በመድን በኩል ከሀቢብ ከማል በተጨማሪ አጥቂው አቡበከር ወንድሙ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል።