ንግድ ባንኮች ኢትዮጵያ መድንን 4ለ1 በመርታት መሪነታቸውን ካጠናከሩበት ጨዋታ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታ አድርጋለች።
“ሰከንድ ሃፍ ላይ ብዙ ነገር አስተካክለን የምንፈልገውን ነገር ማድረግ ችለናል” አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ
“በውጤት ቀውስ ላይ ያለ ቡድን የሚፈጠርበት ችግር ነው የተፈጠረብን” አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ
አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ስለ ጨዋታው…?
“ጨዋታው ቆንጆ ጨዋታ ነበር። ሜዳ ስንገባ አስበን የነበርነውን ነገር ለመተግበር ትንሽ ጊዜ ፈጅቶብን ነበር። የመጀመሪያ አርባ አምስት ላይ እነሱ ተጭነውን ነበር። ተጭነው እንደሚጫወቱም እናውቃለን ምክንያቱም ያለፉትን ጨዋታዎች ስናይ ነጥብ ሚስ ያደረጉበት ጨዋታ ስለነበር ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን እናውቅ ነበር ስለዚህ ጌሙን ከመጀመሪያው ጀምሮ ለመጀመር እና ተረጋግተን ለመጫወት ነበር ያሰብነው ግን አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም። የኳስ መቆራረጦች እንደገናም ደግሞ ነርቨስ የመሆን ነገር ያለመረጋጋት ነገሮች በቀላሉ ፍሎው ያለው እግርኳስ ሌላ ጊዜ እንደምንጫወተው ሳይሆን የመበጣጠስ እና የመዘናጋት ነገር ይታይ ነበር። አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም ቀስ በቀስ ወደ ሪትሙ እየመጣን እያለ ነው የመጀመሪያው አርባ አምስት ያለቀው እና ያን ያህል በጣም ጥሩ ነበርን ብዬ ለመድፈር ያስቸግረኛል። ሰከንድ ሃፍ ላይ ብዙ ነገር አስተካክለን የምንፈልገውን ነገር ማድረግ ችለናል። ኳሱን በመቆጣጠር ፣ በማጥቃቱ ፣ ግብ ጋር በመድረስ እና ጫና በመፍጠር የተሻልን ነበርን እና ስፔሻሊ ሁለተኛውን አርባ አምሥት ሙሉ በሙሉ ዶሚኔት ማድረጋችን ፤ ብዙ የግብ ዕድሎችን መፍጠራችን እና እነኛን ወደ ግብ መቀየራችን የተሻለ ቀን አድርጎልናል ብዬ አስባለሁ።”
ዕረፍት ላይ ያደረጋችሁት የተለየ ነገር ምን ነበር…?
“የመጀመሪያ ነገር ሞቲቬሽን በልጠውን ነበር ሲጀመር አካባቢ እነሱ ከእኛ የተሻለ ተነሳሽነት ነበራቸው ቅድም እንዳልኩት የባለፉት ጨዋታዎች ላይ ሚስ በማድረጋቸው ይህንን ነጥብ በጣም ይፈልጉታል። እኛም ደግሞ ባለፈው ጨዋታ በዲቻ ተሸንፈን ስለነበር ወደ አሸናፊነት መመለስ እንፈልጋለን እና በቁጥር አንድ ደረጃ ፎከስ ያደረግነው ሞቲቬሽናችንን ማስተካከል ነው በተረፈ የታክቲካል ዲሲፕሊን መዘበራረቅ ነበር ማለት ይሄ ተጭነው ማርክ እያደረጉ ምናምን መጫወት ሲፈልጉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እየተጠቀምን ነበር ያንን ነገር ሰብሰብ አድርጎ ውጤታማ የማድረግ ነገር በምን መልኩ እናስተካክል የሚለውን ያው ስትራክቸራል የማድረግ ነገር ላይ ነው ያወራነው ከዛ በተረፈ እንግዲህ የተጫዋች ቅያሪም አደረግን እና ቡድኑን ለማስተካከል ሞከርን ማለት ነው።”
አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን
ስለ ጨዋታው…?
“ሁለት ገጽታ ነው የነበረው። የመጀመሪያው አርባ አምሥት ደቂቃ ከሚገባው በላይ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር ቡድናችን ያሳየው እንቅስቃሴ በሁለተኛው አርባ አምሥት የተወሰነ ጫና ፈጠሩብን ግን አንዳንድ እንደተፈጠሩብን ስህተቶች ያው እንደዚህ ዓይነት በውጤት ቀውስ ላይ ያለ ቡድን የሚፈጠርበት ችግር ነው የተፈጠረብን። ስህተቶች አንዳንዶች አላሳመኙኝም እኔ በሲሙሌሽን እንደውም መቀጣት የሚገባቸው ተጫዋቾች ነበሩ ግን በተቃራኒው ቅጣት ምቶች ይሰጡብን ነበር። እሱ ችግር አለው ያው የዳኛው ይሆናል ግን እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች እንደተፈጠሩ በአንድ ጊዜ ጨዋታው ተቀየረ እና ይኸው ነው የሆነው።”
አጣነው የምትሉት ነገር…
“ከዕረፍት በፊት ያጣነው ነገር አለ ብዬ አላስብም። እንደው አለ ቢባል የበለጠ ስኮር ማድረግ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ አታክ ለማድረግ ነው የገባነው። ደግሞም አጋጣሚዎችን ፈጥረናል እሱን ሚስ ማድረጋችን በራሱ ሌላ ጫና እንዲፈጠር ሆኗል። አንድ ለባዶ ስለነበር ውጤቱን አስፍተን ካልጠበቅን በስተቀር አስቸጋሪ ነው እና እንደዚህ ዓይነት ሁለት የተለያየ ውጤት ያለን ቡድኖች ነን በራስ መተማመኑ በእኛ በኩል የወረደ ነው ፤ በእነርሱ በራስ በመተማመኑ በከፍተኛ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት እና በዚህ ሁኔታ ላይ ስትሆን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው የሚሆነው።”