በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ለይ የሚገኙትን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ ሀምበርቾን 3-0 በሆነ ውጤት በመርታት ከአስር ጨዋታዎች በኋላ የዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀምበርቾ እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ሀምበርቾዎች ባለፈው የአስረኛ ሣምንት ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ ሲያደርጉ በቀይ ካርድ ቅጣት የዛሬው ጨዋታ የሚያልፈውን ብሩክ ቃልቦሬን በአቤል ዘውዱ ሲተኩ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አንድ አቻ የተለያዩት ሻሸመኔዎች በአንጻሩ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ምንተስኖት ከበደ እና ማይክል ኔልሰንን በኤቢሳ ከድር እና ጌታለም ማሙዬ ተክተው አስገብተዋል።
9 ሰዓት ላይ ሁለቱም ቡድኖች የሚፈለገውን ትጥቅ ባለማሟላታቸው ለአራት ያህል ደቂቃዎች ዘግይቶ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በመጠኑ የተቀዛቀዘ የነበር ሲሆን በማጥቃቱ እንቅስቃሴ ግን ሻሸመኔዎች የተሻሉ ነበሩ።
ኳስን በጥልቅ የጨዋታ መንገድም ሆነ ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች ጨዋታውን ከደቂቃ ደቂቃ መቆጣጠር የጀመሩት ሻሸመኔዎች 26ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አብዱልቃድር ናስር ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አለን ካይዋ ካመቻቸለት በኋላ ኳሱን ያገኘው ሄኖክ ድልቢ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ኳሷ በተከላካይ ተጨርፋ መረቡ ላይ አርፋለች። ሻሸመኔዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተሻለ መነቃቃት በፍጥነት ወደ ሀምበሪቾ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር ጥረትን አድርገዋል።
ጥንቃቄ አዘል በሚመስል አቀራረብ በረጃጅም ኳሶች በመጫወት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመድረስ ሀምበርቾዎች ቢጥሩም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት የሻሸመኔን የተከላካይ መስመር ለማለፍ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በይበልጥ ሻል ባሉ ተሻጋሪ ኳሶች ጨዋታውን መቆጣጠራቸውን የቀጠሉት ሻሸመኔ ከተማዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተጨማሪ ጎል አክለዋል። አለን ካይዋ ከተከላካይ ጀርባ ሲጥል የሀምበርቾ ተከላካዮች በግንባር ጨርፈው የሰጡትን ኳስ ምንተስኖት ከበደ ከመረብ አዋህዶ የሻሸመኔን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ሀምበርቾዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸውን ክፍተት ለማረም የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ፀጋሰው ድማሙ ፣ ቶሎሳ ንጉሴ እና የኋላሸት ፍቃዱ ወጥተው በምትኩ በረከት ወንድሙ አፍቅሮት ሠለሞን እና አላዛር አድማሱ ተተክተዋል። አጋማሹን ሀምበርቾዎች ቢጀምሩም በፍጥነት የነጠቁት ሻሸመኔዎች 47ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ፓሉማ ፓጆም ባወጣት ኳስ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።
በረከት ወንድሙ በተሰለፈበት የቀኝ የሜዳው ክፍል ላይ ባዘነበለ መልኩ ከአጥቂው ዳግም በቀለ ጋር በሚደረጉ ንክኪዎች ሀምበርቾዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የመጨረሻው የኳሱ ማረፊያ በእጅጉ ደካማ ሆኖ ታይቷል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ ከማዕዘን አላዛር አሻምቶ አቤል ከቀጀ በግንባር ገጭቶ ኬኒ ሰይዲ ተቆጣጥሮበታል።
በቁጥር ባነሰ የማጥቃት ኃይል በተወሰነ መልኩ ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን በመስጠት ይጫወቱ የነበሩት ሻሸመኔዎች በመከራ ረገድ እዮብ ገብረማርያም ከቅጣት ምት አሻምቶ ለጥቂት ከወጣችበት ውጪ በአጋማሹ ቀዝቀዝ ብለው ታይተዋል። ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በአፍቅሮት እና ዳግም አማካኝነት በድግግሞሽ ሙከራን ሀምበርቾዎች ቢያደርጉም ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ 90+5 ላይ አጥቂው አለን ካይዋ በረጅሙ ከምንተስኖት ከበጀ የደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂው ፓሉማ ፓጆምን መውጣት ተመልክቶ በአናቱ ከፍ በማድረግ አስቆጥሮ ጨዋታው በሻሸመኔ 3-0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል። ድሉም ከአስር ጨዋታዎች በኋላ ሻሸመኔን ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ አድርጓል።