“የዛሬው ጠንካራ ጎናችን የማሸነፍ ፍላጎታችን ነበር” አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ
“በብዙ መልክ ተጎድተናል” አሰልጣኝ መላኩ ከበደ
ሻሸመኔ ከተማ ሀምበርቾን ሦስት ለባዶ አሸንፎ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያው ሦስት ነጥብ ካገኘበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል
አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ሻሸመኔ ከተማ
ስለ ጨዋታው …
“ጨዋታው ከባድ ይሆናል ብለን ገምተን ነበር። ከዕረፍት መልስ ከባድ ነበር፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ግን ጫና ፈጥረን ነው የተጫወትነው። ማሸነፍና ሦስት ነጥብ ማግኘት ያስፈልገን ነበር ፤ ቡድናችን ባለፉት ጨዋታዎች መሻሻሎች አሉት፤ ማሸነፍ አልቻልንም እንጂ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ወጥተናል። ተፎካካሪ ሆኖ በሊጉ ላይ ለመቆየት ልዩነቱን ማጥበብ ችለናል። በአጠቃላይ ውጤቱ በጣም ጥሩ ነው።”
ስለ ቡድኑ የዛሬ ጥንካሬ …
“የዛሬው ጠንካራ ጎናችን የማሸነፍ ፍላጎታችን ነበር። በጨዋታው እንደነበረን ነገርና ያሳየነው ብቃት በቂ ነው ብዬ አላስብም። አንዳንድ ጊዜ ጨዋታውን የሰጠህን ነገር መቀበል አለብህ፤ ተጨማሪ ግቦች የምናስቆጥርበት አጋጣሚ ነበር ያንን መጠቀም ይገባን ነበር። በዛ አንፃር ክፍተት ነበር። ዛሬ ሦስት ነጥብ አገኘን እንጂ ውድድሩ ማራቶን ነው ገና ብዙ ይቀረናል።”
የዛሬው ድል ለቀጣይ ምን ይዞ ይመጣል ?
“ከጨዋታ ጨዋታ ያለን መሻሻል ጥሩ ነው፤ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አልተሸነፍንም። በቀጣይ ጨዋታም በነጥብ ከሚቀራረበን መድን ስለምንጫወት ከፍተኛ መነሳሳት ይፈጥርልናል።”
አሰልጣኝ መላኩ ከበደ – ሀምበርቾ
ስለ ጨዋታው …
“ጨዋታ ጥሩ ነበር፤ ግን እንደጠበቅነው አላገኘንም። በብዙ መልክ ተጎድተናል፤ ከዚህም በላይ ማግኘት ነበረብን። ዕረፍት ሁለት ለባዶ እየተመራን ከወጣን በኋላ ከዕረፍት መልስ የተሻሉ ዕድሎች ፈጥረን ነበር አልተጠቀምንበትም።”
ስለ አጨራረስ ክፍተታቸው…
“ያገኘኸውን አጋጣሚ የማትጠቀም ከሆነ ዋጋ ትከፍላለህ። ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ነበርን ግን ዕድሎች መጠቀም ላይ ትልቅ ችግር አለብን። ቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን። ከዚህ በላይ የተሻለ ነገር ጊዜው ቢረፍድም ለመስራት ወደ ኋላ አንልም።”
ስለ ቡድኑ ክፍተት…
“ቡድኑ በሥነ-ልቦና ረገድ ተጎድቷል፤ ግን ያንን ችግር በትክክል ካከምን ቡድኑ በተሻለ ሊሻሻል ይችላል። በቀጣይ በሥነ-ልባናም ይሁን በሌላ ያለውን ክፍተት አስተካክለን የተሻለ ነገር ለመስራት እንጥራለን።”