በሳምንቱ መቋጫ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ጎል ፋሲል ከነማን 1-0 በመርታት ወደ ድል ተመልሷል።
ከአስረኛ ሳምንት ጨዋታቸው ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋችን ቅያሪ አድርገው በዛሬው መርሀግብር ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ በወልቂጤ ላይ ድል ከቀናው ስብስብ ቃልኪዳን ዘላለምን በይሁን እንዳሻው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ ተለያይተው በነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ጉዳት በገጠመው አቤል ያለው ምትክ አማኑኤል አረቦን ተክተው ቀርበዋል።
አስቀድሞ ከተሰጠው ግምት አኳያ ከጅምሩም ብርቱ ፉክክርን እንደሚያስመለክተን ይጠበቅ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የዕለቱ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካቸው ካሰሙበት ደቂቃ አንስቶ ሜዳ ላይ ከሚደረጉ የኳስ መንሸራሸሮች ውጪ ቡድኖቹ ከጎል ጋር ራሳቸውን ለማገናኘት የሚጓዙበት አቀራረብ ደካማ ነበር። ፈረሰኞቹ በሁለቱ የመስመር ተጫዋቾቻቸው ቢኒያም እና ተገኑ አማካኝነት ከአማካይ ክፍላቸው በሚመነጩ ኳሶች ጎልን ለማስቆጠር የሚሄዱበት ርቀት ከተጋጣሚያቸው አኳያ በይበልጥ ጥራት አይኖራቸውም እንጂ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል።
አፄዎቹ በበኩላቸው ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል በሽግግር የጨዋታ መንገድ በፍጥነት በአንድ ሁለት ቅብብሎች መድረስ የቻሉ ቢመስሉም የጊዮርጊስን የመከላከል አጥር ሰብረው ለመግባት ተቸግረው ተስተውሏል። ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ለማየት የግድ አስራ ዘጠኝ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደናል። በዚህም ደቂቃ ሻል ባለ መልኩ ወደ ጎል በመድረሱ የተዋጣላቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከቀኝ ወደ ውስጥ ሔኖክ አዱኛ ሲያሻግር ቢኒያም በላይ በቀጥታ መትቶ ኳሷ ተደርባ ስትመለስ ተገኑ በድጋሚ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ሳማኪ ሲመልሰው በድጋሚ አማኑኤል አረቦ እግሩ ላይ የደረሰችውን ኳሷ ከግቡ ቋሚ ወደ ውጪ ሰዷታል።
ዓለምብርሀን ይግዛው 32ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር በኩል በጥልቀት ገብቶ ካደረጋት ሙከራ ውጪ እምብዛም የተሳኩ ሙከራዎች ለማድረግ የከበዳቸው ፋሲሎች በተቃራኒው አጋማሹ ሊገባደድ ስምንት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ያለቀላቸው ሙከራዎችን አስተናግደዋል። በቅድሚያ 37ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሳማኪ ሚካኤል ኳስን ለማቀበል የተሳሳተውን ኳስ ዳዊት ተፈራ አግኝቶ ወደ ጎል መትቶ ለጥቂት ኳሷ ወጥታለች። 40ኛው ደቂቃ ላይም ፈረሰኞቹ ጎል ለማስቆጠር በእጅጉ ተቃርበው ነበር። ቢኒያም የሰጠውን ዳዊት በጥሩ ዕይታ በዓየር ላይ ኳሷን ልኳት ተገኑ በግንባር ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ብረትን ጨርፋ ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ግለቱ ከፍ ብሎ የታየ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከቅጣት ምት ዳዊት አሻምቶ ናትናኤል ወደ ጎል መትቶ በተያዘበት አጋጣሚ የፋሲልን የግብ ክልል ቀድመው መፈተሽ ችለዋል። የሜዳ ላይ ፉክክሩ ተመጣጣኝ መልክ ቢኖረውም ጎልን ለማስቆጠር ይሄዱበት የነበረበት ርቀት ግን እምብዛም የተሳካ ነበር ማለት አይቻልም። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከ53ኛው ደቂቃ በኋላ ከቅጣት የተመለሰውን ሞሰስ ኦዶን በዳዊት ተፈራ ተክተው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ በእጅጉ በፋሲል የመከላከል ክፍል ላይ ጫናን ለማሳደር ብዙም አልከበዳቸውም። 63ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲሉ የመስመር ተከላካይ ዓለምብርሀን ይግዛው ተገኑ ተሾመ ላይ የሜዳው መሐል ክፍል ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ከተወገደ በኋላ በይበልጥ በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ ተገደዋል።
በአስር ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት አፄዎቹ አቤል እንዳለ እና ሱራፌል ዳኛቸውን በማስወጣት ቃልኪዳን ዘላለም እና ዮናታን ፍሰሀን ወደ ሜዳ በማስገባት ቡድኑን ለማረጋጋት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የመጨረሻ ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው ጫና የፈጠሩት ጊዮርጊሶች ጎል አስቆጥረዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ ከተከላካዮች እግር ስር ታግሎ ነጥቆ ያቀበለውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ መረቡ ላይ አሳርፏት ቡድኑን መሪ አድርጓል። የተሰጠውን ስምንት ጭማሪ ደቂቃ ለመጠቀም ጫናን ወደ ማሳደሩ አፄዎቹ የገቡ ሲሆን ይሁን እና አምሳሉ ካደረጉት ሙከራ በኋላ ጨዋታው በፈረሰኞቹ 1-0 አሸናፊነት ተቋወጥታለች።