የ2016 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ዛሬ ሲጠናቀቅ በምድብ ‘ሀ’ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተከታዩ ንብ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት አስፍቷል።
ረፋድ 03፡00 በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከትናንት ለዛሬ በይደር ተይዞ በተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ተደርጎበታል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን በተደጋጋሚ በመድረሱ በኩል ኤሌክትሪኮች ብልጫውን በመውሰድ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም የተሻለው ንጹህ የግብ ዕድል ግን በአዲስአበባዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጠር በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን የደረሰው አማኑኤል መሬት ለመሬት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት ይዞበታል።
ከዕረፍት መልስ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ኤሌክትሪኮች አጋማሹ በተጀመረ በ 20 ሴኮንዶች ውስጥ በአቤል ሀብታሙ ግብ ጨዋታውን መምራት ሲጀምሩ በቀሪ ደቂቃዎች ውስጥም ሁለቱም ቡድኖች ለተመልካች ሳቢ ፉክክር ሲያደርጉ 80ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባው ታዳጊ ተጫዋች ቧይ ኩዌት በግሩም አጨራረስ ግብ ቢያስቆጥርም ግቡ ከመቆጠሩ በፊት ጥፋት ተሠርቷል በሚል ረዳት ዳኛው ቀድመው ባንዲራቸውን በማንሳታቸው ግቡ ሊሻር ችሏል። ሆኖም ጨዋታው በተሻለ የራስ መተማመን በነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተከታዩ ንብ በሰባት ነጥቦች በልጦ የውድድር ዘመኑን አጋምሷል።