የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የፋሲል ከነማ አማካይን ለማስፈረም የአሜሪካው ክለብ ጥያቄ መቅረቡ ታውቋል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ በማቅናት የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርጎ መመለሱ ይታወሳል። በወቅቱም ይህንን ጉዞ በተመለከተ የፌዴሬሽን ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በአሜሪካ ቆይታ ዙርያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቢንያም በላይ፣ አቤል ያለው፣ ሽመልስ በቀለ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ማርከስ ቬላዶ-ፀጋዬ እና ሱራፌል ዳኛቸው በተለያዩ ክለቦች መልማዮች ዕይታ ውስጥ የገቡ መሆናቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ከነዚህ ተጫዋቾች መካከል ጋቶች ፓኖም
ሀርት ፎርድ አትሌቲክስ ክለብ የሙከራ ጊዜን አግኝቶ ለቀናት ቆይታ ያደረገ ሲሆን ሙከው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቶ ወደ ሀገር ቤት መመለሱ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ የዚሁ አሜሪካው ጉዞ አካል ሆኖ ሱራፌል ዳኛቸውን ለማስፈረም ሎዶን ዩናይትድ ለፋሲል ከነማ ጥያቄ ማቅረቡን አውቀናል።
ሎዶን ዩናይትድ ሱራፌልን በቀጥታ ለማስፈረም
ፍላጎት እንዳለው እና ከክለቡ አመራሮች ጋር ድርድር እያደረገ መቆየቱን አውቀናል። ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በሎዶን ዩናይትድ እና በፋሲል ከነማ መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር በጥሩ መግባባት እየሄደ ሲሆን የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ሱራፊል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር እንደተጠናቀቀ የካቲት ወር መጀመርያ ላይ ወደ አሜሪካ የሚጓዝ ይሆናል።
ሎዶን ዩናይትድ መቀመጫውን በሊዝበርግ ቨርጂንያ ያደረገና በUCL Championsip የሚካፍል ቡድን ሲሆን የዲሲ ዩናይትድ እህት ክለብ መሆኑ ይታወቃል።