ትናንት ማለዳ የዕረፍቱን ዜና የሰማነው የአንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) የግል እና የሥራ ህይወትን በአጭሩ ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ስለትውልዱ…
አንጋፋው ታሪክ አዋቂው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በትናንትው ዕለት ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል። መጋቢት 5 ቀን በ1957 በይርጋለም የተወለደው ጋዜጠኛ ገነነ የበዛ የልጅነት ጊዜውን ወዳሳለፈባት ሻሸመኔ ከተማ አቅንቶ በአፄ ናኦድ ትምህርት ቤት የመጀመርያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮን ነበር ገነነ የመፃፍ እና እግርኳስ የመጫወት ፍቅሩ ያደረበት።
የመፃፍ ችሎታውን ያዳበረበት መንገድ…
የቡና ነጋዴ የነበሩት አባቱ አቶ መኩርያ ገቢና ወጪያቸውን የሚፅፉበት መዝገብ ሲሞላ አባቱ ይሰጡታል። ታዲያ ገነነ አዲስ ዘመን እና ስፖርት ፋና ጋዜጦችን እየተቀበለ በማዞር ገንዘብ ከመቀበል ይልቅ ለሠራበት አንድ ጋዜጣ በነፃ እየተቀበለ የማንበብ ልምዱን እንዳዳበረ እና ፎቶዎቹን ከጋዜጣዎቹ እያወጣ በመዝገቡ ላይ እያስቀመጠ እና ያነበበውን ፅሑፍ በራሱ መንገድ እየጻፈ ለሰፈር ጓደኞቹ እያከራየ በማስነበብ የፅሑፍ ችሎታውን ማሳደግ ችሏል። ገነነ ጋዜጣን ማንበብ እና መፃፍ ብቻ ሳይሆን ወደ እግርኳሱ በማዘንበል ይጫወት እንደነበረ የታሪክ ድርሳኑ ያመለክታል።
የገነነ የእግርኳስ ተጫዋችነት ሕይወቱ…
ገነነ መኩርያ አምስት ወንድሞች ሲኖሩት አምስቱም እግርኳስን ተጫውተው ያለፉ መሆናቸው ይነገራል። እንዳውም በአንድ ቡድን ውስጥ በዝተው ስላሉ የቀበሌያቸው ቡድን 09 ከመባል ይልቅ ‹የአቶ መኩሪያ ቡድን› ነበር የሚባለው። ገነነ ከሁሉም ወንድሞቹ በልዩነት ለሲ ቡድን አጥቂ ፣ ለቢ ቡድን አማካኝ ፣ ለኤ ቡድን ግብ ጠባቂ ሆኖ በመጫወቱ ሁለገብ ተጫዋች ተብሎ ብርሌ መሸለሙ ይነገራል። ገነነም አረንቻታ ለሚባል የሰፈር ቡድን በግብ ጠባቂነት የጀመረው የእግርኳስ ሕይወቱ በመቀጠል ነበልባል ለሚባል ቡድን ተጫውቷል። ከቀይ ሽብር በኋላ ወጣቱን በስፖርት ለማቀፍ በወጣው ፖሊሲ ተጠቃሚ በመሆን ለሻሸመኔ በተለያዩ አውራጃዎች ከታችኛው እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በግብ ጠባቂነት መጫወት ችሏል። በማስከተል በ1974 በሀምሳ ብር ወርሀዊ ደመወዝ ከግብ ጠባቂነት ግልጋሎቱ ወጥቶ አውራ ጎዳና ለተባለ ክለብ ተጫዋች ሆኖ እያገለገለ ባሳየው ምርጥ ብቃት በ1975 ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለሜታ ቢራ በመጫወት የኢትዮጵያ ሻምፒዮን መሆን እንደቻለ ታሪኩ ያስረዳል። ገነነ ለመብራት ኃይል የተጫወተ ቢሆንም ተደጋጋሚ የመሰለፍ ዕድል በማጣቱ ከ1980 እግርኳሱን በማቆም ወደ ጋዜጠኝነቱ አዘንብሎ መስራት ጀምሯል። ገነነ (ሊብሮ) ከእግርኳስ ተጫዋችነቱ ባሻገር በሩጫ እና በጠረንጴዛ ቴኒስ ስፖርት ይጫወት እንደነበረ የሕይወት ታሪኩ ያመለክታል።
የገነነ መኩርያ (ሊብሮ) የጋዜጠኝነት ህይወት…
እግርኳስን እየተጫወተ እግረ መንገዱን በተግባረ ዕድ የሙያ ትምህርት በመማር በጄኔራል መካኒክነት የተመረቀው ገነነ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከ1978 ጀምሮ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለያዩ ፅሑፎችን ማቅረብ ጀመረ እንዲህ እያለ የቀጠለው የፅሑፍ ሥራው ለተለያዩ ጋዜጦች እና መፅሔቶች ፅሑፉን ማቅረብ ቀጥሎ የካቲት ለተሰኘ መፅሔት እየተከፈለው መሥራት ጀመረ። በእጁም በእግሩም የሚታትር ትጉህ የሆነው ገነነ በሁለት የሚወዳቸው ነገሮች ስለከፈሉት ደስተኛ እንደነበረ ይነገራል።
ገነነ በማስከተል እግርኳስን አቁሞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ጋዜጠኝነቱ አምርቶ መርሐ ስፖርት ለተሰኝ ጋዜጣ መፃፍ ከመጀመሩ ባሻገር ለብሥራት ወንጌል ራዲዮ ፕሮግራም ላይ ይሳተፍ ነበር። በኋላ ላይ ወደ ግል ሥራዎቹ በማተኮር ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ሻምፒዮን የተሰኘ ጋዜጣ በመመስራት መፃፍ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ራሱን ችሎ ሊብሮ የተሰኘ ጋዜጣ መስርቶ ለአስራ ሦስት ዓመታት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ስራዎቹን ለትውልዱ ሲያስተላልፍ ቆይቷል። በኢትዮጵያ በእግር ኳስ ተጫዋችነት፣ በጋዜጠኝነት የሚታወቀው ገነነ ወደ በመጻሕፍት ደራሲነት በመሻገር ኢህአፓ እና ስፖርት ፣ መኩርያ ፣ ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል። ወደ ራዲዮውም ዳግም በመመለስ ለዓመታት በብሥራት ኤፍ ኤም ከመሰለ መንግስቱ ጋር የማይሰለቹ ታሪኮችን በቀልድ እያዋዛ ዕውቀትን ሲያስተላልፍ መቆየቱም አይዘነጋም።
ገነነ መኩሪያ በአሻም ቲቪ ትኩረታቸውን በስፖርት እና በታሪክ ላይ ያደረጉ “የገነነ” እና “ጥቁር እንግዳ” የተሰኙ ፕሮግራሞችን ለዓመታት በአዘጋጅነት እና አቅራቢነት ሲሠራ መቆየቱም ይታወቃል። የሙዚቃ ዕውቀቱ ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገርለት ገነነ በ97 ኤፍ ኤም ከአዲስ ዜማዎች ጋር ለዓመታት መሥራቱ አይዘነጋም።
ለገነነ መኩሪያ “ሊብሮ” የሚለው ቅፅል መጠሪያው እንዴት ሊወጣለት ቻለ ?
ተወዳጁ ሚድያ እና ኮሚዩኒኬሽን “መዝገበ አዕምሮ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ የተሰነደው የገነነ መኩሪያ ግለ-ታሪክ እንደሚያስረዳው ነገሩ እንዲህ ነው፦
በ1978 ይካሄድ ለነበረ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የእርስ በእርስ ግጥሚያ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሜታ ቢራ በአንድነት ካረፉበት ገነት ሆቴል ፤ ኃይሌ ካሴ የተባለ የጊዮርጊስ ተጫዋች ከአንድ የሜታ ቢራ ተከላካይ ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ ያወራል። የሜታው ተጫዋች እነ ቤከን ባወርን እየጠቀሰ “ሊብሮ” ስለሚባለው የአጨዋወት መንገድ ለኃይሌ ካሴ በስሜት ያስረዳዋል። በማግስቱቱ … ለኃይሌ ካሴ ገለፃ ሲያደርግ የነበረው የሜታ ቢራው ተከላካይ ከኋላ ተነስቶ፣ ግብ ጠባቂውን ጨምሮ አራት የጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ግብ ያስቆጥራል። የሜታው ተከላካይ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ደስታውን ገልፆ ወደ ሜዳው ሲመለስ ኃይሌ ካሴ ወደ ተከላካዩ ጠጋ ብሎ፥ “ሊብሮ ያልከኝ ይሄ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል። የሜታው ተጫዋችም በፈገግታ “አዎ” ሲል ይመልስለታል። የሜታ ቢራው ተከላካይ ፈገግታውን እንኳን ሳይጨርስ በዚህ ቅፅበት “ሊብሮ” የሚል ቅፅል ስም ይወጣለታል። የዛኔው የሜታ ቢራ ተከላካይ ዛሬ ስሙን ከመቃብር በላይ ትቶ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና የእግር ኳስ ተጫዋቹ ገነነ መኩሪያ ነው። “ሊብሮ” የተሰኘው ቅፅል ስሙ የአያቱን ስም ተክቶ ባሳለፋቸው የሜዳም፣ የሚዲያም ታሪኩ ውስጥ ከፍ ብሎ ተጠርቶበታል – ገነነ መኩሪያ ሊብሮ።
ገነነ ያገኛቸው የክብር ሽልማቶች…
ለእግር ኳስ ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦም በ2009 በአዲስ አበባ በተሰናዳው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አገልግሎት ሜዳሊያ ተበርክቶለታል። ይህንንም ሽልማት ያገኘ በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው ጋዜጠኛ ያደርገዋል። ስፖርት ዞን የራዲዮ ፕሮግራም በአንድ ወቅት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጎት እንደነበረም ይታወቃል።
የገነነ የቤተሰብ ህይወት…
ታላቁ ጋዜጤኛ ገነነ ከወ/ሮ አስቴር ጋር የትዳር ህይወቱን በመጀመር የአንድ ወንድ እና የአንድ ሴት ልጆች አባት ሲሆን በቤተሰቦቹ የሚከበር የሚወደድ መሆኑ ሲነገር ሁለቱም ልጆቹ በትምህርት የላቀ ደረጃ እንዲደርሱ ብርቱ ጥረት ያደርግ እንደነበረ ሲታወቅ ወንድ ልጁ ናኦም ገነነ የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል አግኝቶ በአሁኑ ሰዓት በሀገር ውስጥ የማይገኝ ሲሆን ሴት ልጁ ኤሊኦም እዚሁ በመሆን ትምህርቷን በጥሩ ደረጃ እየተከታተለች መሆኑን አውቀናል።
የታላቁ ጋዜጠኛ የቀብር ሥነ ስርዓት ዛሬ ጥር 15 ቀን በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በዘጠኝ ሰዓት ወዳጅ ዘመዶቹ የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት ተፈፅሟል።
ሶከር ኢትዮጵያ በድጋሚ የታላቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ሕልፈተ ሞት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ ፣ ለወዳጆቹ እና ለመላው የስፖርት ቤተሰብ መፅናናትን ትመኛለች።