በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ11ኛ ሳምንት ከተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ነጥረው የወጡ ተጫዋቾችን በ4-3-3 አደራደር በምርጥ ስብስብ እንዲህ መርጠናል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ፋሲል ገብረሚካኤል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ብዙም ግብ ጠባቂዎች ባልተፈተኑበት የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት ሻል ያለ የጨዋታ ጊዜን ያሳለፈው የፈረሰኞቹ የግብ ዘብ ቡድኑ ፋሲልን ባሸነፈበት ጨዋታ የግብ ክልሉን በንቃት የጠበቀመበት መንገድ በሳል መሆኑን ተከትሎ የምርጥ ስብሰባችን አካል አድርገነዋል።
ተከላካዮች
ምንተስኖት ከበደ – ሻሸመኔ ከተማ
ሻሸመኔ ከተማ የናፈቀውን ሦስት ነጥብ ወደ ቋቱ በከተተበት ሳምንት ከተሰጠው የመከላከል ሚናው በይበልጥ ወደ ፊት በመሳብ ቡድኑ አሸፎ እንዲወጣ አንድ ጎል በማስቆጠር እና ለሦስተኛዋ ግብ መገኘት መነሻ መሆኑን ተከትሎ በተከላካይ አደራደራችን ውስጥ ተካቷል።
አስቻለው ታመነ – መቻል
መቻል ድሬዳዋን 3ለ1 በረታበት ጨዋታው የመሐል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ግልጋሎቱ ቀላል የማይባል ነበር። ተጋጣሚ ቡድን የመረጠውን ተሻጋሪ ኳሶች ከማስጣል አንስቶ ወደ ቀኝ መስመር በማዘንበል በመከላከሉ ጥሩ የሜዳ ጊዜን አሳልፏል።
ፈቱዲን ጀማል – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ድራማዊ በሆነ የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ ሲመራ የነበረው ንግድ ባንክ ውጤቱን ቀልብሶ 4ለ1 መድንን ሲረታ የፈቱዲን አስተዋጽኦ ትልቁን ቦታ ይይዛል ከመሐል ተከላካይነቱ በተጨማሪ ቡድኑ ወደ ጨዋታ እንዲመለስ ተጫዋቹ ከቅጣት ምት የተገኙ ሁለት ኳሶችን በግንባር አስቆጥሮ ቡድኑን ባለ ድል ማድረጉ ተከትሎ በምርጥነት ልናካትተው አስችሎናል።
ደስታ ዮሐንስ – ሲዳማ ቡና
ክለቡን በአምበልነት እና በግራ መስመር ተከላካይነት እየመራ ባህርዳርን ቡድን ሲያሸንፍ ከመከላከል ሚናው በተጨማሪ በማጥቃት ሂደቱ ላይ ጉልበት በመጨመር ቡድኑ ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች በማቀበሉ የተዋጣለት ነበር።
አማካዮች
ሐብታሙ ንጉሴ – ሻሸመኔ ከተማ
ሻሸመኔዎች የናፈቃቸውን የድል ረሃብ ባስታገሱበት የሳምንቱ ጨዋታ የሀብታሙ ሚና ከፍተኛ ነበር። ሐብታሙ የቡድኑን የመሐል ሜዳ ክፍል በአግባቡ በመሸፈን እንዲሁም በመከላከሉ ረገድ ያሳየው ትጋት እና የከፈለው መስዋዕትነት በምርጥ ስብስብን ውስጥ ልናካትተው አስችሎናል።
በኃይሉ ግርማ – መቻል
ሚዛናዊ የሆነ የመሐል ሜዳ ክፍል ሽፋን ከመስጠት በተጨማሪ ድሬዳዋ ከተማ መቻልን 3ለ1 ሲያሸንፍ ሁለተኛ ጎልን ማስቆጠሩ እና በቦታው ጥሩ የጨዋታ ሳምንት ማሳለፉ አስመርጦታል።
ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ከጨዋታ ጨዋታ ማስገረም የማይሰለቸው ጋናዊው አማካይ በ11ኛ ሳምንቱም ጎምርቶ ታይቷል። መድን ላይ ባንክ ድል ባደረገበት ጨዋታ ለአጥቂ ክፍሉ ጥራት ያላቸውን ኳሶች ሲያቀብል የነበረው እና በመጨረሻም አዲስ እና ቢኒያም ላስቆጠሯቸው ግቦች ኳስን አመቻችቶ ሰጥቷል።
አጥቂዎች
አለን ካይዋ – ሻሸመኔ ከተማ
ዩጋንዳዊው የፊት መስመር አጥቂ ሻሸመኔ ከሀምበሪቾ ላይ የዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ሲያገኝ ሜዳ ላይ ለተከላካዮች ፋታን ከማይሰጡ እንቅስቃሴዎቹ በተጨማሪ ሔኖክ ድልቢ ላስቆጠራት ኳስ አመቻችቶ ሲሰጥ ሦስተኛዋንም ጎል ከመረብ አሳርፏል።
ተባረክ ሄፋሞ – ሀዋሳ ከተማ
ሀዋሳ ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ድል ሲያደርግ የአጥቂው ሚና ቀላል አልነበረም። የተጋጣሚ ቡድንን የግብ ክልል ሲያስጨንቅ ቆይቶ ጎልንም ያስቆጠረው ተጫዋቹ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ መከላከሉ መጥቶ የድቻን የአየር ላይ ኳሶች ሲያፀዳ መታየቱ ልናካትተው አስችሏል።
ኢዮብ ዓለማየሁ – ሀዋሳ ከተማ
ሀዋሳ ድቻን 2ለ1 ረቶ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ የመስመር አጥቂው እዮብ የቀድሞው ክለቡ ላይ ጫናን በሚያሳድሩ ፈጣን እንቅስቃሴዎቹ እንዲሁም ተባረክ ላስቆጠራት ጎል ወደ ግብ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂን ከፈተነበት ሙከራው በዘለለ ሁለተኛዋን ጎል ማስቆጠሩ አስመርጦታል።
አሰልጣኝ
በፀሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በጨዋታ ሳምንቱ ለተመልካች በተለየ መልኩ በሳቢነቱ የሚወሳው የኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ንግድ ባንክ ከዕረፍት በፊት 1ለ0 ሲመራ ቆይቶ ከዕረፍት በኋላ ግን ከጨዋታ ብልጫ ጋር አራት ግቦችን በማስቆጠር 4ለ1 አሸንፎ እንዲወጣ የአሰልጣኙ የታክቲክ ለውጦች ከፍ ያሉ በመሆናቸው በምርጥ አሰልጣኝነት ስብሰባችን ውስጥ ሊመረጡ ችለዋል።
ተጠባባቂ
አሊዮዚ ናፊያን
ፍሪምፓንግ ሜንሱ
ሠለሞን ወዴሳ
አሸናፊ ጥሩነህ
በረከት ግዛው
አዲስ ግደይ
ተገኑ ተሾመ