የ12ኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።
ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሰባት ነጥቦች ልዮነት በሰንጠረዡ አንደኛ የሚገኙትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች የሚያገናኘው የዕለቱ ተጠባቂ መርሃግብር ዘጠኝ ሰዓት ሲል ጅማሮውን ያደርጋል።
እንደ ቡድን በመጨረሻ ሶስት የሊግ ጨዋታዎች በውጤት ረገድ መቀዛቀዝ ውስጥ የገቡት የጣና ሞገዶቹ ከእነዚሁ ጨዋታዎች ማግኘት ይገባቸው ከነበረው ዘጠኝ ነጥብ ማሳካት የቻሉት ሁለቱን የመሆኑ ነገር ለአሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው ሆነ ለስብስባቸው የሚያስጨንቅ ጉዳይ ነው።
አሁን ላይ በ19 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻ ሶስት ጨዋታቸው ሁለት ቀይ ካርድን የመመልከታቸው ጉዳይ ከአጋጣሚነት ባለፈ ምናልባት ቡድኑ ውስጥ ስላለው ውጥረት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በነገው ጨዋታ ወሳኙን ተከላካያቸውን ያሬድ ባየህን በቅጣት የማያገኙ ሲሆን ከመሪዎቹ ጋር እየሰፋ የመጣውን የነጥብ ልዮነት ለማጥበብ ከሦስት ነጥብ በላይ ትርጉም በሚኖረው የነገው ጨዋታ ባህር ዳሮች ለማሸነፍ ያላቸውን ሁሉ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሽንፈት በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት ሳይጠበቁ በወላይታ ድቻ እጅ ቢያስተናግዱም በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን 4-1 በሆነ ውጤት በመርታት በፍጥነት ወደ ቀደመው የአሸናፊነት መንገዳቸው የተመለሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አሁን ላይ በ26 ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት ይገኛሉ።
በክረምቱ በርከት ባሉ አዳዲስ ተጫዋቾች የተዋቀረው ቡድኑ በአጠረ ጊዜ የተዋሀደ ቡድን ሆኖ እየተመለከትን ስንገኝ አሁን ቀጣዩ ፈተና የሚሆነው ሰንጠረዡን ከፊት ሆነው እንደመምራታቸው የሚኖረውን የተጠባቂነት ስሜት እንዴት ያስተናግዱታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
የነገውን ጨዋታ ጨምሮ በቀሪ የመጀመሪያ ዙር መርሃግብሮች ከፋሲል ከነማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጋር ጠንካራ መርሃግብሮች የሚጠብቃቸው ንግድ ባንኮች እነዚህን ፈተናዎች እንዴት ሊወጡ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ላይ ካለው ከተከላካዩ ፍቃዱ ደነቀ በስተቀር ሙሉ ቡድን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።
ሁለቱን ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኘውን ይህን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ወጋየሁ አየለ አራተኛ ዳኛ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሆኗል።
አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ
የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ደግሞ በሶስት ነጥብ ልዮነት 9ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን አዳማን ከሀዋሳ የሚያገናኝ ይሆናል።
የመጨረሻ ድላቸውን ካስመዘገቡ አምስት የጨዋታ ሳምንት ያስቆጠሩት አዳማ ከተማዎች በተጋጣሚ መረብ ላይ ግብ ካስቆጠሩም እንዲሁ ሶስት የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል ፤ ታድያ ቡድኑ አሁን ድረስ ይህን የአስቆጣሪነት ሚና የሚወስድ ሰው በጥብቅ እየፈለገ ያለ ይመስላል።
15 የአንደኛ ዙር መርሃግብሮችን በመቀመጫ ከተማቸው የማድረግ ዕድልን ያገኙት አዳማ ከተማዎች አጀማመራቸው መልካም የነበረ ቢመስልም አሁን ላይ ግን በደጋፊያቸው ፊት ነጥብ ለመያዝ እየተቸገሩ ይገኛል ፤ ይህም ደካማ ጉዞ ለመቀልበስ እና ዙሩን በተሻለ መልኩ ለመቋጨት ነገን ጨምሮ በሚኖራቸው ቀሪ ጨዋታዎች ከደጋፊያቸው አብዝተው የሚጠብቁ ይሆናል።
በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈትን በማስተናገድ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የሰነበቱት ሀዋሳ ከተማ እና አሰልጣኛቸው ዘርዓይ ሙሉ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ታግዘው ወላይታ ድቻን 2-1 በመርታት በመጠኑም ቢሆን ተንፈስ ያሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
ለማመን በሚከብድ መልኩ በሊጉ ጅማሩ በተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን የማያስደፍር የመከላከል ውቅር ባለቤት የነበረው ቡድን በሂደት ይህን ጥንካሬውን አጥቶ የተመለከትነው ሲሆን በቀጣይ ነጥቦችን ከጨዋታዎች ይዞ ለመውጣት በዚህ ረገድ አሁንም መሻሻል ይኖርባቸዋል።
ሀዋሳ ከተማዎች ይህን ከአምስት ጨዋታ በኃላ የተገኘውን ድል ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉበት በሚጠበቀው በነገው ጨዋታ ከቡድኑ ጋር በተለያየ ምክንያት አብረው ከማይገኙት ሙጂብ ቃሲም እና ሚሊዮን ሰለሞን ውጭ ከጉዳትና ከቅጣት ነፃ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ለነገው ጨዋታ ሲቀርቡ በአንፃሩ በአዳማ ከተማ በኩል አማካዩ አልያስ ለገሰ እና ተከላካዩ ሀቢብ መሀመድ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ43 ጊዜያት ያህል ተገናኝተው ሀዋሳ 19 አዳማ ደግሞ 12 ጊዜ ሲያሸንፉ 12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ጎል በሚበረክትበት የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ሀዋሳ ከተማ 50፣ አዳማ ከተማ 45 ጎሎች አስቆጥረዋል።
የምሽቱን መርሀግብር ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በዋና ዳኝነት አብዱ ይጥና እና አዲሱ ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ ረዳቶች ሀይማኖት አዳነ በአንፃሩ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።