የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን መካተቱን ካፍ አሳውቋል።
የ2023 ስያሜን እንደያዘ በቀጣዩ ወር የሚደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በጋና አስተናጋጅነት በዋና ከተማዋ አክራ ይከናወናል። በውድድሩ ላይ በሁለቱም ፆታ ሀገራት የሚካፈሉ ሲሆን የካፍ ኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴም በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ የሴት ብሔራዊ ቡድኖችን ይፋ ባደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዝርዝሩ አካቷል።
ከየካቲት 29 ጀምሮ እስከ መጋቢት 15 ድረስ እንደሚደረግ ቀን የተቆረጠለት ውድድር ላይ በ2022 በኮስታሪካ ተደርጎ በነበረው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ላይ ተካፋይ ለመሆን በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን ያደረጉ ቡድኖች የተካተቱ ሲሆን እስከ መጨረሻው የአራተኛ ዙር ድረስ የተጓዘችው ኢትዮጵያንም ተሳታፊ እንዳደረጋት ታውቋል። በውድድሩ ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ናይጄሪያ ፣ ሴኔጋል ፣ ካሜሮን ፣ ሞሮኮ ፣ ታንዛኒያ ፣ ዩጋንዳ እና አስተናጋጇ ሀገር ጋና ይገኙበታል።