በሣምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመመራት ተነስቶ ባህር ዳር ከተማን 2ለ1 መርታት ችሏል።
ተጠባቂ በነበረው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲገናኙ የጣና ሞገዶቹ በ11ኛው ሣምንት በሲዳማ ቡና 2-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ፍጹም ፍትሕዓለው ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ መሳይ አገኘሁ እና ዓባይነህ ፌኖ በያሬድ ባዬህ ፣ አብዱላዚህ ሲያሆኔ ፣ ረጀብ ሚፍታህ እና ፍጹም ጥላሁን ተተክተው ገብተዋል። ንግድ ባንኮች በአንጻሩ በተመሳሳይ ሣምንት ኢትዮጵያ መድን ላይ የ 4ለ1 ድል ሲቀዳጁ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሱሌይማን ሐሚድ ፣ ካሌብ አማንክዋህ እና ሀብታሙ ሸዋለም አርፈው በብሩክ እንዳለ ፣ ዮናስ ለገሠ እና ቢኒያም ጌታቸው ተተክተዋል።
የአንጋፋውን ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ሕልፈት አስመልክቶ የሕሊና ጸሎት ከተደረገ በኋላ 9፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የፊሽካ ድምፅ አማካኝነት በተጀመረው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ገና በ3ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቸርነት ጉግሣ በግሩም ክህሎት በሳጥኑ የግራ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ በእንዳለ ዮሐንስ ጥፋት ተሠርቶበት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አለልኝ አዘነ አስቆጥሮታል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሚያገኟቸው ኳሶች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች 10ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ፍሬው ሰለሞን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው የአብሥራ ተስፋየ ያደረገውን ሙከራ የመሃል ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ሲያግድበት በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ አለልኝ አዘነ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር በሚያደርጉት ዝግ ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ የተስተዋሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 27ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ባሲሩ ኦማር ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ በተከላካይ ሲመለስ ያገኘው ኪቲካ ጅማ በግራ እግሩ ወደ ግብ ቢመታውም ሲጨረፍበት ያኑን የተጨረፈ ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ይመስል የነበረው ቢኒያም ጌታቸው አግኝቶት በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግቡ በተቆጠረበት ቅጽበትም የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች በረዳት ዳኛው ወጋየሁ አየለ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ጨዋታውን ሲጀምሩ ወደ ነበራቸው ግለት የተመለሱት የጣና ሞገዶቹ 32ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሣ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አግዶበታል። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 41ኛ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስመለክተን እጅግ ተቃርቦ ነበር። ሀብታሙ ታደሠ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። ይህም የአጋማሹ የተሻለ የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስመልከት 13 ደቂቃዎችን ጠብቋል። ሆኖም 58ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳሩ ሀብታሙ ታደሠ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ይዞበታል።
ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተለይም ከአማካዩ ባሲሩ ኦማር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መታተራቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 64ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ግዛው በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ባሻገረው ኳስ የግብ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ በስድስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ታምራት ከረጅም ርቀት ያሻገረለትን ኳስ የባህር ዳር ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው በተዘናጉበት ቅጽበት የተቆጣጠረው አዲስ ግደይ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ አመቻችቶ ያደረገውን ሙከራ በግብ ጠባቂው እና በግቡ የላይ አግዳሚ ሲመለስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ባሲሩ ኦማር በግንባር በመግጨት ያደረገውን ሙከራም ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በድጋሚ መልሶበታል።
ጨዋታው 73ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ንግድ ባንኮች ከሦስት ደቂቃዎች በፊት ከፈጠሩት ንጹህ የግብ ዕድል ፍጹም ተመሳሳይ በሆነ ሂደት ጎል አስቆጥረዋል። በረከት ግዛው ከመሃል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ በፍጥነት ሾልኮ በመውጣት የተቆጣጠረው አዲስ ግደይ እየገፋ በመውሰድ እና ከግብ ጠባቂው ጋር በመገናኘት በግሩም አጨራረስ ግብ አድርጎታል።
የአቻነት ግብ ከተቆጠረባው በኋላ መልስ ለመስጠት ሲጥሩ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ቀይረው ያስገቡትን አጥቂውን ሱሌይማን ትራኦሬን ባስተናገደው ጉዳት ምክንያት በይኸነው የማታ ለመተካት ሲገደዱ የተደራጀ የማጥቃት እንቅሰቃሴ ለማድረግም ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ንግድ ባንኮች ነጥባቸውን 29 በማድረስ መሪነታቸውን አስጠብቀዋል።