አምስት ግቦችን በተመለከትንበት በምሽቱ አስደናቂ ጨዋታ አዳማ ከተማ 3-2 በሆነ ውጤት ሀዋሳ ከተማን በመርታት ከራቀው ድል ጋር ተገናኝቷል።
በምሽቱ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ አዳማዎች በ11ኛው ሣምንት ከወልቂጤ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሱራፌል ዐወል እና ቦና ዓሊ በሀቢብ መሐመድ እና ነቢል ኑሪ ተተክው ገብተዋል። በተመሣሣይ ሣምንት ወላይታ ድቻን 2ለ1 የረቱት ሀዋሳዎች በአንጻሩ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ ተባረክ ሔፋሞን አሳርፈው ታፈሰ ሰለሞንን አስገብተዋል።
ፈጠን ያሉ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ባስተዋልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአመዛኙ መሐል ሜዳ ላይ በይበልጥ ትኩረትን ያደረጉ አጨዋወቶች የተበራከቱበት ነበር። አዳማ ከተማ ኳስን ተቆጣጥረው መሐል ላይ ብልጫን በመያዝ ወደፊት ተስበው ሲጫወቱ ብንመለከትም የሀዋሳን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ግልፅ የግብ ዕድልን በመፍጠሩ የተዋጣላቸው አልነበሩም። በአንፃሩ የዓሊ ሱለይማንን ፍጥነት ተጠቅመው በሽግግር ለመጫወት የሚጥሩት ሀዋሳዎች በዚሁ አጨዋወታቸው ከተከላካይ ጀርባ በተጣለ ኳስ ዓሊ አምልጦ ወጥቶ ወደ ጎል የመታውን እና ተከላካዮች ተደርበው ባወጧት አጋጣሚ ሀዋሳዎች በሙከራ ቀዳሚ ሆነዋል። በፈጣን መልሶ ማጥቃት መጫወታቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች ዳግም ተጨማሪ ሙከራ አድርገዋል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ከአዳማ ተከላካዮች የነጠቀውን ኳስ ለታፈሰ ሰጥቶ አማካዩ ከጀርባው ለነበረው እዮብ ሲሰጠው ተጫዋቹ መሬት ለመሬት የመታት ኳስ ሰይድ ሀብታሙ ያዳነበት ሌላኛዋ ጥራቷን የጠበቀች በሀዋሳ የተደረገች ሙከራ ሆናለች።
የጨዋታ ፍጥነት እና ግለት ቀጥሎ አዳማዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል የሚፈጥሩትን ክፍት ቦታዎች ሀዋሳዎች ለመጠቀም ጥረት ያደረጉበትን አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ለማጥቃት በፍጥነት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የሀዋሳን ጥቅጥቅ ያለ መከላከል በማለፉ ረገድ ግን አሁንም ስኬታማ አልነበሩም። ጨዋታው 39ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሯል። ከተከላካይ ጀርባ የተጣለን ኳስ ተከላካዩ አህመድ ረሺድ እና ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ለማውጣት ሲገባበዙ ዓሊ ሱለይማን አምልጦ ወጥቶ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፏታል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት ሁለት ደቂቃ ብቻ የፈጀባቸው አዳማዎች ወደ አቻነት መጥተዋል። ቦና ዓሊ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቀኝ ወደ ግራ መሬት ለመሬት የሰጠውን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ በቀላሉ አስቆጥሮ 1ለ1 በሆነ ውጤት አጋማሹ ተገባዷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ብዙም ሳይጓዝ ጎል ተመልክተናል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ታረቀኝ ራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት መቶ ቻርለስ ሉክዋንጎ መረብ ላይ በማሳረፍ አዳማን መሪ አድርጓል። ጎል ማስተናገዳቸው ተከትሎ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ተግባራዊ በማድረግ ሀዋሳዎች በሁለት አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎችን በዓሊ አማካኝነት ፈጥረዋል። በመጀመሪያ ሙከራ ዓሊ ከመሐል ሜዳ የግብ ጠባቂው ሰይድን ከጎል ክልሉ መውጣቱን ተመልክቶ ወደ ግብ ሲመታ አህመድ ረሺድ በግንባር ያወጣበት እና በድጋሚ ሌላ ጥራት ያላት ሙከራን አድርጎ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት እጅግ የሚያስቆጩ ሙከራዎቻቸው የነበሩ ሲሆን ጥረታቸውም ሰምሮ ግብ አግኝተዋል።
59ኛው ደቂቃ አዲሱ አቱላ ከረጅም ርቀት ወደ ግብ የላካትን ኳስ ተከላካዮች ደርበው ስትመለስ እዮብ አለማየሁ አክርሮ ወደ ግብ መቶ ጨዋታውን ወደ 2ለ2 አሸጋግሯል። ለወትሮው ግቦች በማያጣው የቡድኖቹ ጨዋታ ድራማዊ በሆነ እንቅስቃሴ ታጅቦ ቀጥሎ የስታዲየሙ ፓውዛ ለአርባ አንድ ሰከንዶች ጠፍቶ ከተመለሰ በኋላ አምስተኛ ጎልን ተመልክተናል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም አይተን ተጫዋቾችን በመቀነስ ያሻገረለትን ኳስ ቦና ዓሊ አዳማን ወደ 3ለ2 መሪ ያደረገችን ጎል በግንባሩ አስቆጥሯል። በግብ የተንበሸበሸ ምሽትን ያስመለከተን ጨዋታ በጥሩ ፉክክር መቀጠል ቢችልም በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች እንቅስቃሴዎቹ እየተቋረጡ ወደ መጨረሻ ደቂቃ አካባቢም በድጋሚ የስታዲየሙ መብራት ጠፍቶ ከተመለሰ በኋላ ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።