ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠባቂው ጨዋታ ባህርዳር ከተማን 2ለ1 በመርታት የሊጉን መሪነት ካጠናከረበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።
አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እየተመሩ ማሸነፋቸው እና ስለዛሬው ጨዋታ…
“ለዛሬ ጨዋታ ካደረግናቸው ዝግጅቶች ውስጥ አንደኛው ባህርዳር ከተማ በጣም ጠንካራ ከምንላቸው ሁሉም ጠንካራ ናቸው ግን ባህርዳር ከተማ ደግሞ በጣም ጠንካራ ከምንላቸው ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። የተጫዋች ኳሊቲ ፣ ጥልቀት እንደገና ደግሞ ሊጉም ላይ ለዋንጫ ከሚፎካከሩ ቡድኖች ውስጥ አንዱ እንደመሆኑ መጠን ከዚህ በተጨማሪም እኛም መሪ ላይ ስለነበርን እኛን አስጥለው ወደፊት ለመጠጋት የሚያደርጉትን ጥረት እናውቅ ነበር። እኛ ደግሞ በተቃራኒው ያለንን ለማስቀጠል እንዲሁም ጠንካራ እንደመሆናቸው ምን አይነት ዝግጅት ማድረግ አለብን የሚለውን በጥልቀት አይተን ነበር የመጣነው ፣ በተለይ በመስመር የሚጫወቱትን ጨዋታቸው በጣም አደገኛ እንደሆነ እናውቅ ነበር ፣ ያንን ለመዝጋት ሞክረናል ፣ እንደገና ደግሞ በዛው አድቫንቴጅ እንዳያገኙ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሁለቱም ፉልባካቸውን ፣ የመስመር አጥቂዎቹ እንደገናም ፊት ላይ ፣ ሚድፊልዳቸውም በጣም ጠንካራ የምትላቸው ፓርታቸው ነው። በተለይ መሐል ሜዳውን ዶሚኔት ማድረግ ፣ መስመራቸውን ማቆም በአንፃሩ ደግሞ እኛ ኳስ ተቆጣጥረን መጫወት የበለጠ ተጭነን የግብ ዕድሎችን መፍጠር ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምረን ለማድረግ ሞከርን ግን እንደ አጋጣሚ ገና አንድ ደቂቃ ከምናምን አካባቢ ይመስለኛል ጎል ተቆጠረብን ይሄ ማለት ፔናሊቲው ያ ትንሽ ቶሎ ሪትም ውስጥ እንዳንገባ አድርጎናል ፣ ምክንያቱም እዛ አካባቢ ላይ በተለይ ቀኝ ፉልባኩ እንዳይረጋጋ ከታች ያደገ ልጅም እንደመሆኑ መጠን ነርቨስ የመሆን ነገር ነበረበት ፣ ከዛ ድጋሚ ጥፋት የመስራት ነገር ስላየሁበት ወዲያውኑ ያንን ለማስተካከል ሱለይማን ገባ በይበልጥ ማጥቃቱም ላይ አጀማመራችንን ማስተካከል ፣ መጀመሪያ ጥሩ አልነበረም ኳስን ስንጀምር የመጀመሪያ የሜዳው ክፍላችን ላይ እና ያንን የማስተካከል መሐል ሜዳውን ማኔጅ የማድረግ ከዛ በኋላ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በተረጋጋ መልኩ መግባት የሚለው ነገር ነበር ፣ ለማስተካከል ሞክረን እንግዲህ ይህንን ነጥብ ይዘን ወጥተናል።”
ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ተለውጠው ስለቀረቡበት መንገድ…
“በመጀመሪያ በስነ ልቦናው ረገድ ኮንፊደንሳችንን ማምጣት ነበር። በዕርግጥ የዘጠኝ ሰዓት ጨዋታ እውነት ለመናገር ለሁሉም ክለቦች ይከብዳል ፣ በጣም ዐየሩ ብዙም የሚመች አልነበረም ፣ በጣም ሙቀት ነበረው በዚህ ሙቀት ውስጥ ይሄን ቴምፖውን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ማለት ማኔጅ ማድረግ በጣም በከፍተኛ ኢንቴንሲቲ ብቻም ሳይሆን ባላንሱን እየጠበክም መሄድ የሚፈልግ ነበር ፣ ይመስለኛል አንደኛው ኢፌክት ቶሎም ሪትም ውስጥ እንዳንገባም ካደረገን አንዱ ነው። ግን በሁለተኛው አጋማሽ ላይ እነርሱ ትንሽ ወረድ የማለት ነገር እኛ ደግሞ የመጨመር ፍላጎትን ነበር ያሳየነው በስነ ልቦናው የመብለጥ ጨዋታውን ተረጋግቶ መጫወት አንደኛው የሜዳ ክፍል ፣ ሁለተኛው የሜዳ ክፍል ፣ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያሉት ምን ይመስላሉ የሚለውን የማስተካከል ስራ ነው ዕረፍት ላይ ያደረግነው ቅያሪን ጨምሮ ማለት ነው። በይበልጥ ያንን ለማየት ሞከርን ክፍተታችንን ፣ የእነርሱን ጠንካራ ጎን ፣ ደካማም ጎን ለማየት ሞከርን ዕረፍት ላይ ያንን አስተካከልን ተሳክቶልናል። ጎል እንድናገባ ረድቶናል ፣ እንደገና ደግሞ ጨዋታውን ሜኔጅ እንድናደርግ ረድቶናል።”
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህርዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው …
“ጠንካራ ጨዋታ ነው የዘጠኝ ሰዓት ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ከሜዳም ከዐየር ንብረቱም ጋር አብረህ የምትጫወተው ጨዋታ ነው እንደ ተጋጣሚህ ጥንካሬ ፣ ሆኖም የጎል ቅድሚያውን ወስደን የተሻለ እየተንቀሳቀስን በነበረበት ሰዓት ያገኙት የአቻነት ጎል ግን የጨዋታውን አጠቃላይ ድባብ ቀይሮታል ብዬ አስባለሁ። እንደነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ተጫዋቾቻችን የሚችሉትን ያህል ጥረት አድርገዋል። ጥሩ ለመጫወት እየሞከርን ነው ያለነው እንዳየህው ትንሽ የስኳድ ጥበትም አለ ፣ እንደ ቡድን ለማስተካከል እንኳን አንዳንድ ጊዜ በሚያስቸግር ሁኔታ ሆኖም ግን ሜዳ ላይ የነበሩ ተጫዋቾች የሚችሉትን ያህል አድርገዋል።”
ከዕረፍት በኋላ ስለ ተወሰደባቸው ብልጫ እና ለማስተካከል ሳላደረጉት ጥረት…
“የመሐል ሜዳውን ብልጫ ለማስተካከል የመከላከል ባህሪ ያለው ሁለተኛ አማካይ ተጫዋች ለመክተት የሞከርንበት ሁኔታ ነበር ፣ ምክንያቱም የመሐል ሜዳውን ብልጫ ስትወስድ ነው ጨዋታውን መቆጣጠር የምትችለው ነገር ግን ባሰብነው ልክ ሄዶልናል ብዬ ባላስብም እንደ ቡድን የተሻለ ነገር ለማድረግ ጥረት የተደረገበት ጨዋታ ነበር የነበረው። ጎሎች ያስተናገድንበት መንገድ ትንሽ ምቾት የሚሰጡ አይደሉም። እንደ አጠቃላይ እንደ ቡድን ብዙ ስራ እንደሚጠይቀን እናውቃለን በቀጣይ ጊዜያትም የተሻለ ሰርተን ፣ የተሻለውን ባህርዳር ከተማ ይዘን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን።”
አዲስ ግደይ በቀኝ በኩል በተደጋጋሚ በመሳይ አገኘሁ በኩል ጥቃቶችን መሰንዘሩ…
“ግልፅ ነው ይሄንን ለማስተካከል ከጨዋታው በፊትም ተነጋግረንበት የገባነው ነው። ጎሎች ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ ምን እንደሆነ ቀድመን ተዘጋጅተንበት ነው የገባነው ፣ እንዳየህው ግን በጨዋታ የመመሰጥ ነገር ፣ በእንቅስቃሴም የመመሰጥ ነገርን ነው የምታየው ፣ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለ ኳስ ነው ሁለተኛ ጎልን የተጠቀሙት እና እዚህ ላይ ትንሽ ጨዋታን የማንበብ ችግርን ታያለህ ፣ ፓፔ ብቅ ብሎ ኢንተርሴቭት ማድረግ የሚችለው ኳስ ነበር። ከዛ ውጪ ግን ሁልጊዜ እንደዚህ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች ሲኖሩ ስፔስ ሰጥተህ ነው መከላከል ወይም ታይት ማርክ አድርገህ መቋቋም የማትችለውን እንቅስቃሴ ብልጥ መሆን ይጠይቃል። እዚህ ላይ ተሸውደናል ብዬ አስባለሁ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ልጆቻችን አውቀዋል ፣ ያንን ለመከላከል ሲሞክሩ ቆይተዋል ግን ተደጋጋሚ ጥረቶቻቸው ተሳክቶላቸው ያንን ዕድል ፈጥረዋል።”