በ12ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት ሊጉ ዳግም በቀጥታ ስርጭት ሽፋን በሚያገኝበት ዕለት የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ
የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ከወሳኝ ድል የተመለሱትን ፈረሰኞቹን አሰልጣኝ ከቀየሩት ብርቱካናማዎቹ ያገናኛል።
እንደ ቀደሙት ዓመታት በተወሰነ መልኩ በወጥ ብቃት ለመጓዝ እየተቸገሩ ያሉት ፈረሰኞቹ በመጀመሪያዎቹ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ካሳኳቸው ተከታታይ ድሎች በኋላ ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ ለማሸነፍ የተቸገሩ ይመስላል። ፋሲል ከነማ ላይ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተው የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት እጅግ አስደናቂ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን ከመግጠማቸው በፊት በሚያደርጉት የነገው መርሃግብር ከመሪው ጋር ያላቸውን የስምንት ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የነገው ጨዋታ የላቀ ትርጉም እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ከቀናት በፊት ከዋና አሰልጣኛቸው ከነበረው አስራት አባተ ጋር በስምምነት የተለያዩት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁን ላይ በጊዚያዊነት የአስራት ምክትሎች በነበሩት ኮማንደር ሽመልስ አበበ እና ዓለምሰገድ ወ/ማሪያም ከቴክኒካል ዳይሬክተራቸው ጋር በመሆን በጣምራ ቡድኑን በቀጣይ ጨዋታዎች እንደሚመሩ ይጠበቃል።
በሊጉ በጣምራ ሁለተኛው ደካማው መከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆኑት ድሬዳዋ ከተማዎች ከአዳዲሶቹ አሰልጣኞች ጋር በቂ የዝግጅት ጊዜ ባይኖራቸውም ይህን ደካማ የመከላከል መዋቅር መፍትሄ ማበጀት ቀዳሚው የቤት ሥራቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።
በውድድር ዘመኑ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎች ብቻ በድል የተወጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በየዓመቱ የውድድር ዘመኑ መገባደጃ ላይ በሰንጠረዡ ግርጌ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ራሳቸውን ማግኘት የተላመዱት ቢመስልም አሁን ላይ በ11 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ርቆ የሚገኘው ቡድን ዘንድሮ ወደዛ ትግል እንዳያመራ የአሰልጣኝ ሹም ሽሩ መልካም ዜናን ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ ተደርጓል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በፋሲል ከነማው ጨዋታ ያልነበረው አቤል ያለው በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ሲታወቅ በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ላይ ከሚገኙት ተመስገን ደረሰ እና ያሲን ጀማል በተጨማሪ አሰጋኸኝ ጴጥሮስም ከነገው ስብስብ ውጭ ሲሆን ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርልስ ሙሴጌ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ ስለማገገሙ ማረጋገጥ ችለናል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ22 ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14ቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 3ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። ፈረሰኞቹ 38፣ ብርቱካናማዎቹ 16 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ባህሩ ተካ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ማዕደር መረኝ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በአራተኛ ዳኝነት በጣምራ ጨዋታውን ይመሩታል።
ሲዳማ ቡና ከ ሀምበርቾ
የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ በሰንጠረዡ ወገብ የሚገኙትን ሲዳማ ቡናዎችን በሰንጠረዡ ግርጌ ከሚገኙት ሀምበርቾዎች የሚያገናኝ ይሆናል።
ደካማ የሊግ አጀማመር ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች በሂደት በተለይም የአሰልጣኝ ሹም ሽር ካደረጉ በኋላ በብዙ መልኩ የተሻሻለ ጉዞን እያደረጉ ሲገኝ አሁን ላይ በ15 ነጥቦች በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ይገኛሉ።
ከመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታቸው ሦስቱን በአሸናፊነት ያጠናቀቁት ሲዳማ ቡናዎች በተለይ ደግሞ በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግዱ የመውጣታቸው ጉዳይ ስለ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ተፅዕኖ በሚገባ የሚያሳይ ነው። ነገም በወራጅ ቀጠናው ላይ ከተቀመጠው ሀምበርቾ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለመውሰድ የተሻለ ቅድመ ግምትን አግኝተው ወደ ጨዋታ የሚገቡ ሲሆን እዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድረስ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካት ያልቻሉት ሀምበርቾዎች በሊጉ እስካሁን በስምንት ጨዋታዎች ተረተው በሦስት የአቻ ውጤት በሰበሰቡት ሦስት ነጥብ በሰንጠረዡ ግርጌ ይገኛሉ።
በብዙ መልኩ መሻሻሎችን የሚሻው ቡድን 18 ግቦችን በማስተናገድ የሊጉ ደካማው መከላከል ባለቤት ሲሆን በአማካይ በአራት ጨዋታ አንድ ግቦችን የሚያስቆጥረው የቡድኑ ማጥቃት እንዲሆ በሊጉ ደካማው ነው። በአሰልጣኝ መላኩ ከበደ የሚመራው ስብስቡ ከአስተዳደራዊ ፈተናዎቹ ባሻገር በሊጉ ለማቆየት ከበላያቸው ከሚገኙ ክለቦች ያለው ልዩነት ይበልጥ ሳይሰፋ ከወዲሁ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በሲዳማ ቡና በኩል ወሳኙ ተከላካያቸው ጊት ጋትኩት አምስተኛ ቢጫ ካርዱን በመመልከቱ ሳቢያ እንደማይኖር ሲረጋገጥ በሀምበርቾዎች በኩል ተከላካያቸው ቴዎድሮስ በቀለ በግል ጉዳይ መነሻነት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬ ደግሞ በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል።
ይህን ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው መስፍን ዳኜ ሲዳኘው ወጋየሁ አየለ እና አብዱ ይጥና ረዳቶቹ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተሰይሟል።