“ለተመልካችም ለተጫዋቾችም ጥሩ ጨዋታ ነበር” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ
“ቡድናችን እውነት ለመናገር እንደዛሬው ተጫውቶ አያውቅም” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ
በምሽቱ አስደናቂ ጨዋታ አዳማ ከተማ 3ለ2 በሆነ ውጤት ሀዋሳን ከረታ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ነበራቸው።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታው እጅግ ጥሩ ጨዋታ ነበር። ሽንፈት ባይገባንም ግን ብዙ ኳሶችን አመከንን ወደፊት ስንሄድ እጅግ በጣም ጥሩ ነበርን እስከ አሁን ከነበረን ጨዋታ እጅግ ውቡ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል እና ጥቃቅን ስህተቶች ኋላ ላይ ትንሽ ዋጋ አስከፈለን እንጂ ቡድናችን እውነት ለመናገር እንደዛሬው ተጫውቶ አያውቅም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥሯል መጠቀም ትንሽ ቢቀረውም ግን እንደ ቡድን የቡድኔ እንቅስቃሴ በጣም የሚገርም ነው። ግን አንዳንዴ እንደዚህም ተጫውተህ ትሸነፋለህ በዚህ አዝኛለሁ ቡድኔ ሽንፈት አይደለም አቻ አይገባውም ግን ምን ታደርጋለህ እግር ኳስ ነው። ከዛ ውጪ ስለዳኝነቱ ብዙ ባላወራ ጥሩ ነው ፣ ስለ ዳኝነት ዝምታን መርጣለሁ ምክንያቱም በተደጋጋሚ ጫናዎች አሉብን ግን ባልናገር መርጣለሁ።”
ከመሩ በኋላ ወዲያው ጎል ያስተናገዱበት ምክንያት …
“ቶሎ ለመከላከል አለመደራጀታችን ትንሽ እርሱ ዋጋ አስከፍሎናል ግን ተጨማሪ ጎሎችን የምናገባ የሚመስለው እንቅስቃሴያችን ፣ ቶሎ ጎሉን ካገባን በኋላ ሁለቱንም ጎል አይተህ ከሆነ ያገቡብን እና ቶሎ ሳንደራጅ ነው። በዕረፍት ተነጋግረን ነበር ቶሎ መደራጀት አለብን የሚለውን ግን በዚህ ስሜት አቋቋም ሁለተኛውም ተቆጥሮብናል ዞሮ ዞሮ እግር ኳስ ነው ለእኛ ባይገባንም የዛሬውን ሽንፈት በፀጋ እንቀበላለን።”
ዓሊ ሱሌይማን በተደጋጋሚ ብስጭት ውስጥ ይገባ የነበረው እገዛ በማጣት ወይስ…?
“ዓሊ በተደጋጋሚ ያልፋቸዋል ከኋላ ጥፋቶች ይሠሩበት ነበር። በተደጋጋሚ ዳኛው ላይ ነው ምክንያቱም በፍጹም ሊጠብቀው አልቻለም። ይሄዳል ይጣላል ፋውል ይሠራበታል በዚህ የተነሳ ነው እንጂ ጎል ዓሊ እየታጀበ ነው ጎል ጋር እየደረሰ ያለው በፍጥነት ነው ጎል ጋር የሚደርሰው እና ለጎል የሚሆን ኳስ የሚያደርሱ አማካዮችም ተከላካዮችም ያንን እያደረጉ ስለነበር ፣ ብስጭቱ ጎልን ለማግባት ነው ሁለተኛ ደግሞ እነዛን ጫናዎች በዳኛው ላይ ነበር ሲያደርግ የነበረው በዚህ ነው ሲበሳጭ የነበረው።”
ከድል ወደ ሽንፈት መምጣታቸው ቡድኑን ጫና ውስጥ ይከታል ማለት ይቻላል…
“በፍጹም ምክንያቱም ቡድኑ በነበረው እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችለው አድርጓል። ምንም የሚያስጨንቅ ነገር የለውም የምትፈራው ቡድኑ ጥሩ ካልሆነ ነው። ስለዚህ ቡድንህ ጠንካራ ከሆነ ፣ በእንቅስቃሴ የተሻለ ከሆነ ነገ እንደምታሸንፍ ስለምታውቅ ምንም የምታዝንበት ተስፋ የሚያቆርጥበት ነገር የለም ነገ ወደ አሸናፊነት ስለምትመለስ።”
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
“ሁሌ ጎሎች ሲኖሩ ጥሩ ፉክክር ይኖራል ፣ ለተመልካችም ለተጫዋቾችም ጥሩ ጨዋታ ነበር ብዬ ነው የምገልጸው።”
ከተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ማሸነፍ መቻላቸው…
“ውድድሩ ገና ነው እያልክ እያመለጠህ እየሄደ ነውና አንዳንዴ አላገቡም ብለህ ቤንች የምታደርጋቸው ተጫዋቾች ዋጋ ያስከፍሉሀል እና እኔ ትልቁ ያየሁበት እና እንደ ልምድም የተጠቀምኩበት ነገር እነዚህ ታዳጊ ልጆችን ደጋግመህ ደጋግመህ ስታስገባቸው ዛሬ ወደ ጎል ተመልሰዋል እና በጣም ነው ደስ ያለኝ አጥቂዎቹ በማስቆጠራቸው።”
የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ላይ መሻሻሎች መታየታቸው…
“የተለየ ነገር የለውም በትዕግሥት እንዲጫወቱ እና እዛች ጋር ረጋ እንዲሉ ነው የምትነግራቸው አጥቂዎቹ ደግሞ ታዳጊ ልጆች ናቸው እና ከዚህ በላይ መሄድ ይችላሉ። አንዳንዴ እንደሌላው ተጫዋች ጫና ላይሸከሙ ይችላሉ ያንን ጫና ተቋቁመው ዕርግጠኛ ሆነው ነው የገቡት ዛሬ ለቋቸዋል ብዬ ነው የማስበው።”
በመጨረሻ ደቂቃዎች በመከላከሉ ጥሩ መሆናቸው….
“ከጨዋታ ጨዋታ እያሻሻልክ የምትመጣቸው ነገሮች አሉ ኮቺንግ ሁሌ በተለይ እኔ ተማሪ ነኝ በትምህርት ውስጥ የምታሻሽላቸው ነገሮች አሉና ትላንት ያጠፋህውን ጥፋት ዛሬ አታጠፋም። አንዳንዴ እነኚህን ልምዶች እየወሰድኩኝ ወደፊት ደግሞ ከዚህ የተሻለ ለመስራት ነው የምሞክረው ተከላካይ ላይ ዛሬ አጠናክሬ ነው የገባሁት ወደ መጨረሻ አካባቢ።”