አሰልጣኛቸውን ያሰናበቱት ብርቱካናማዎቹ በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-0 በሆነ ውጤት ፈረሰኞቹን በመርታት የዓመቱ አራተኛ ድላቸውን አሳክተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት ፋሲልን የረታው ስብስቡን ሳይለውጥ ዛሬም ሲቀርብ በመቻል ሽንፈት ገጥሟቸው በነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በኩል በአንፃሩ የሦሰት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ካርሎስ ዳምጠው ፣ ሙኸዲን ሙሳ እና ያሬድ ታደሠ አርፈው ሱራፌል ጌታቸው ፣ አቤል አሰበ እና ቻርለስ ሙሴጌ በቋሚ አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል።
ከቀናት በፊት ህይወቱ ላለፈው አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የዕሊና ፀሎት ተደርጎ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግብን ያስመለከተን ገና 14ኛው ሰከንድ ላይ ነበር። ኳስን ከመሐል ሜዳ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ከግራ በኩል ወደ ውስጥ መሐመድ አብዱለጢፍ ያሻማለትን ሐይል የለሽ ምትን ተጠቅሞ ኤፍሬም አሻሞ ወደ ግብ ሲመታ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ለመያዝ በሞከረበት ወቅት ኳሷ አምልጣው መረቡ ላይ አርፋ ድሬዳዋን ቀዳሚ አድርጓል። ቅፅበታዊ ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ተቃራኒ ሜዳ በመድረስ አልያም ከተከላካይ ጀርባ ለአጥቂ በሚጣሉ ኳሶች ፈረሰኞቹ ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተወሰነ መልኩ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
12ኛው ደቂቃ ሔኖክ አዱኛ ከማዕዘን አሻምቶ ክዋሜ ፍሪምንግ በግንባር ገጭቶ አብዩ ካሳዬ መያዝ የቻላት እና ከአምስት ደቂቃዎች መልስ ደግሞ ከቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ምክሮ የግቡ ቋሚ ብረትን ኳሷ ገጭታ የወጣችባቸው አጋጣሚ ቡድኑ አከታትሎ ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎቻቸው ነበሩ። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን በመስጠት ነገር ግን በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብን ከማስቆጠር ያልቦዘኑት ብርትኳናማዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስን ፍፁም ብትንትን ያለውን የመከላከል መዋቅር ተጠቅመው ሁለተኛ ጎልን ወደ ቋታቸው ከተዋል። 19ኛው ደቂቃ ከራስ ሜዳ አቤል አሰበ በፍጥነት ያገኘውን ኳስ እየነዳ የጊዮርጊስ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ደርሶ ወደ ቀኝ ያቀበለውን ኳስ ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ ሳይቸገር ወደ ግብነት ለውጧታል።
የመጫወት ፍላጎታቸውን ከፍ በማድረግ መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁንም የቅዱስ ጊዮርጊስን ፍፁም መዘናጋት ተጠቅመው የጎል መጠናቸውን ከፍ ያደረጉበትን ተጨማሪ ግብ አክለዋል። በመከላከል አደረጃጀት ወቅት የአቋቋም ስህተትን በጨዋታው ያዘወተሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 22ኛው ደቂቃ ኤልያስ ከሳጥን ውጪ ኳስን ሲመታ ተከላካዩ አማኑኤል ጨርፏት የደረሰችውን ቻርለስ ወደ ውስጥ ነፃ ቦታ ለነበረው ሱራፌል ጌታቸው ሲሰጠው አማካዩ የግብ ጠባቂው ፋሲል የአቋቋም ስህተት ጭምር ታክሎበት ድሬዳዋን ወደ 3ለ0 መሪነት ያሸጋገረች ግብ አድርጓታል። ዳዊት ተፈራን 33ኛው ደቂቃ ላይ በሞሰስ ኦዶ በመቀየር የአጥቂ ቁጥራቸው ከፍ በማድረግ ፈረሰኞቹ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢጥሩም በአጋማሹ ጎልን ሳያገኙ በድሬዳዋ 3ለ0 በሆነ ውጤት ተጋምሷል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ በእጅጉ ወረድ ባሉ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በሙከራዎች እምብዛም ሳይታጀብ በሁለተኛው አጋማሽ በቀጠለው ጨዋታ ድሬዳዋ በይበልጥ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ጥንቃቄን መርጠው ነገር ግን ኳስን ሲያገኙ በሽግግር ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሂደት ክዋሜን በበረከት በመለወጥ መሐል ሜዳውን በማሻሻል ለመንቀሳቀስ የጣሩበት ቢሆንም ቡድኑ ለማጥቃት ያደርግ የነበረበት ተነሳሽነት ግን ደካማ ነበር ማለት ይቻላል።
ከሙከራ የራቀው እና የተቀዛቀዙ ስሜቶች በሜዳ ላይ ተንፀባርቆ በቀጠለው ጨዋታ ፈረሰኞቹ 65ኛው ደቂቃ ሔኖክ አዱኛ ፣ ተገኑ ተሾመ እና ቢኒያም በላይን በአማኑኤል እንዳለ ፣ ሀሮን አንተር እና አላዛር ሳሙኤል በመተካት ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚመስልን ቅያሪን በማድረግ በተጋጣሚ ላይ ጫናን ለማሳደር ጥረት ሲያደርጉ መመልከት ቢቻልም ቡድኑ በማጥቂያ ዞን ውስጥ የነበረው ፍፁም ደካማ አፈፃፀም ግቦችን እንዳያገኙ ያደረጋቸው ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች በተቃራኒው ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ሦስት ነጥብን ይዞ ለመውጣት በታታሪነት ተጫውተዋል። በአጋማሹ 89ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ድሬዳዋ በሔኖክ አንጃው አማካኝነት ከተደረገች እና የግቡ አግዳሚ ብረት ከመለሰበት ሙከራ ውጪ ጥራት ያላቸውን ዕድሎች ሳንመለከት ጨዋታው 3ለ0 በሆነ ውጤት አሰልጣኝ አሰናብቶ በጊዜያዊ አለቃው ሽመልስ አበበ በተመራው ድሬዳዋ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ብናውቅም ምንም የማይሸንፍበት ምክንያት የለም ብዬ ነበር ከጨዋታው በፊት ካሉ በኋላ ተጋጣሚ ይመጣበታል ያልነውን ቦታ ዘግተን ተዘጋጅተን መጥተን ውጤት ይዘናል ያሉ ሲሆን ቡድኑ ውስጥ ከጅምሩ የነበረው በተጫዋቾች ላይ የሚታየው ፍላጎት እና ተነሳሽነት ግን ለውጤቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል። በአንፃሩ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጥሩ ያልሆነውን ቅዱስ ጊዮርጊስ አይቻለሁ ካሉ በኋላ ጥሩ አይደለንም ጥሩ የሆነው ድሬዳዋ አሸንፎ ወጥቷል ፣ ማግባት እንችል ነበር ቀድማ የተቆጠረችዋ ጎል ከኮንሰንትሬሽን ውጪ አድርጋናለች ካሉ በኋላ ለውጤቱ ኃላፊነት ወስዳለሁ ድሬዳዋ ከተማን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በመጨረሻም ቡድናቸው በቀጣይ መስተካከል እንዳለበትም ጭምር በንግግራቸው ጠቁመዋል።