ዘንድሮ ከታችኛው ሊግ በማደግ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየተሳተፈ ያለው ክለብ የቅዱስ ጊዮርጊሱን አጥቂ ለማስፈረም ከተጫዋቹ ጋር የተስማማ ሲሆን የክለቡ ምላሽም ይጠበቃል።
በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከሁለተኛው የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን በማደግ እየተወዳደረ የሚገኘው ዜድ እግር ኳስ ክለብ በአሀኑ ሰዓት ባደገበት ዓመት የግብፅ ፕሪምየር ሊግን በ19 ነጥቦች እየመራ የሚገኝ ሲሆን ይህም ክለብ ኢትዮጵያዊውን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ አቤል ያለውን ለማስፈረም ከተጫዋቹ ጋር ከስምምነት ስለመድረሱ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እስከ ዓመቱ መጨረሻ ኮንትራት ያለው ተጫዋቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ ከአልሀሊ ጋር እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብፅ ላይ ጨዋታዎቻቸው ባደረጉበት ወቅት በሜዳ ላይ የነበረውን እንቅስቃሴ ክለቡ ተመልክቶ ሊያስፈርመው ስለመስማማቱ የተጫዋቹ ወኪል አዛርያስ ተስፋፂሆን እንዲሁም ራሱ አቤል ያለው ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል።
ተጫዋቹ እንደተናገረው ከሆነ ከክለቡ አሰልጣኝ ማግዲ አብዱል አታይ ጋር በማውራት ከክለቡ ጋር መስማማት እንደቻለ የነገረን ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስም ተጫዋቹ የሚለቅ ከሆነ ከግብፁ ክለብ ዜድ ዳጎስ ያለ የዝውውር ገንዘብን እንደሚያገኝም ጭምር ታውቋል።
ከሁለት ቀናት በኋላ በሚዘጋው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ዝውውር አቤል ያለው ተሳክቶለት የሚያመራ ከሆነ ከሳላሀዲን ሰዒድ ፣ ሽመልስ በቀለ ፣ ዑመድ ኡኩሪ እና ጋቶች ፓኖም በመቀጠል አምስተኛው በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የሚጫወት ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ይሆናል።