በምሽቱ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3-0 በመርታት የዓመቱን ሰባተኛ ድልን አሳክቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባህርዳሩ የባለፈው ድል የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጓል። እንዳለ ዮሐንስን በካሌብ አማንኩዋ ፣ ዮናስ ለገሠን በሱለይማን ሀሚድ ሲተኩ በድሬዳዋ ሽንፈትን አስተናግደው በነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ዳዊት ተፈራ እና ፍሪምፓንግ ኩዋሜ አርፈው ባህሩ ነጋሽ ፣ በረከት ወልዴ እና ሞሰስ ኦዶ በቋሚነት ጀምረዋል።
ከተሰጠው ከፍተኛ ግምት አኳያ ወረድ ባለ መጠነኛ ፉክክር ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በይበልጥ ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመግባት የሚደረጉ ጥረቶችን ያስተዋልንበት ቢሆንም ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች በበቂ ሁኔታ ግን ለመመልከት አልታደልንም። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ያሳዩን ቢሆንም የኳስ ፍሰቶቻቸው ተቃራኒ ሜዳ ላይ ሲደርስ የሚያደርጉት የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው እምብዛም ነበር ማለት ይቻላል። 18ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ እንዳለ ከርቀት መትቶ ባህሩ ሳይቸገር ከያዛት ሙከራ ውጪ በሽግግር የጨዋታ መንገድ የቀረቡት ንግድ ባንኮች ከወትሮ የማጥቃት ይዘታቸው ወረድ ማለታቸው በበቂ ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል መፈተን እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
በተሻለ ተነሳሽነት በቀላሉ የተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ሳይቸገሩ ይደርሱ የነበሩት ፈረሰኞቹ 14ኛው ደቂቃ ላይ ጥራት ያላትን ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ቢኒያም እና ሔኖክ ተቀባብለው ሔኖክ የሰጠውን ከቀኝ የሜዳ የሳጥኑ ክፍል ያገኘው አማኑኤል በቶሎ መቶ ፍሬው ጌታሁን ኳሷን አውጥቶበታል። እንደነበራቸው ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ከጎል ጋር ለመገናኘት ተቸግረው የቆዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ ያገኙት የነበረው የቆመ ኳስ መጨረሻ ላይ ፍሬ አፍርቶ መሪ የሆኑበትን ግብ 39ኛው ደቂቃ ላይ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ተገኑ ላይ በተሰራ ጥፋት ከግራ የሜዳው ክፍል የተገኘን የቅጣት ምት ሔኖክ ወደ ሳጥን ሲያሻማ ናትናኤል ተቆጣጥሮ ወደ ውስጥ በግራ እግሩ የላካትን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ሳይቸገር መረብ ላይ አስቀምጧታል።
የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ግብ እንዳይቆጠርባቸው ለንግድ ባንክ ተጫዋቾች አስቸጋሪ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል አጋማሹ ሊገባድ በጭማሪ ደቂቃ ፈቱዲን ከቅጣት ምት ሞክሮ የፈረሰኞቹ የግብ ዘብ ባህሩ ከተቆጣጠረባቸው አጋጣሚ በኋላ ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 መሪነት ተጋምሷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በኳስ ቁጥጥሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሻል ቢሉም በድግግሞሽ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ንግድ ባንኮች ብልጫውን ወስደዋል። አዲስ ግደይ ከግራ የሜዳ ክፍል በተሻጋሪ ከኪቲካ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በወጣችበት አጋጣሚ የጊዮርጊስን የግብ ክልል መፈተሽ ጀምረዋል።
ወደ መስመር ባጋደሉ ተንጠልጣይ ኳሶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 52ኛው ደቂቃ ከሔኖክ አዱኛ የነጠቀውን ኳስ ኪቲካ ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ ለበረከት ሰጥቶት አማካዩ ባልተረጋጋ ሁኔታ ላይ ሆኖ ቢመታም ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች። ጥንቃቄ ላይ ትኩረትን በማድረግ የንግድ ባንክን የሚጣሉ ኳሶች በአግባቡ ሲቆጣጠሩ የነበሩት ፈረሰኞቹ 63ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሌላ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።
በረከት ከቅጣት ምት አሻምቶ ካሌብ በግንባር ገጭቶ ባህሩ ከመለሠባቸው በኋላ ንግድ ባንኮች በተከታታይ ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ አጥተዋል። 73ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማን ሀሚድ በሳጥን ውስጥ ተጠልፌያለሁ ብሎ መውደቁን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሆን ብለህ ነው የወደከው በማለት በሁለት ቢጫ በቀይ ከሜዳ አስወጥተውዋል።
ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ንግድ ባንኮች ሁለተኛ ተጫዋቾቻቸውን በቀይ አጥተዋል። ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ኳስን ከግብ ክልል ውጪ ወጥቶ ከዳግማዊ እግር ስር በእጅ መመለሱ ተከትሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ ወጥቷል።
ፍሬው ከወጣ በኋላ አዲስ ግደይ በግብ ጠባቂው ፓልክ ቾል ተተክቶ ከአንድ ደቂቃ መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለተኛ ግብን በተከላካዩ ፍሪምፓንግ ሜንሱ አማካኝነት አግኝተዋል። ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ካጡ በኋላ የጊዮርጊስን ጫና መቋቋም የተሳናቸው ንግድ ባንኮች መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ 90+7 ላይ ፓልክ ቾል ለፈቱዲን ወደ ግራ ያቀበለውን ኳስ ጫና ውስጥ በመክተት ዳግማዊ አርዓያ ከተከላካዩ እግር ስር ነጥቆ ወደ ሳጥን ገፍቶ የሰጠውን ወጣቱ ሀብቶም ገብረእግዚአብሔር ወደ ግብነት ለውጦት ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 3ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በመጀመሪያው አርባ አምስት መጥፎ እንዳልነበር ቡድናቸው ገልፀው ወደሪትም እንዳይገቡ የመጀመሪያው ጎል መቆጠር እንዳደረጋቸው በሁለተኛው አጋማሽ ግን ተስተካክለው ቀርበው የነበረ ቢሆንም ከቀይ ካርዱ በኋላ ሁሉም ነገር መበላሸቱን እና በፈለጉት ልክ ቡድናቸው እንዳይሄድ መሆኑን ተናግረው በዳኝነቱ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ግን ለኮሚሽነሮች ትቼዋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቻቸው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በባለፈው ጨዋታ የኮንሰንትሬሽን ችግር እንደነበር እና ከዛ ሽንፈት ለመውጣት በተጫዋቾች አዕምሮ ላይ መስራታቸውን ጠቁመው ውጤቱ በዚህ መንገድ መምጣቱን ገልፀው የታክቲክ ለውጥም ጭምር አድርገው ገብተው ውጤት በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ጭምር አክለዋል።