“በኢትዮጵያ በፊፋ ደረጃ ሰው ሰራሽ ሜዳ ብቸኛ ነው” ፉአድ ኢብራሂም

የድሬደዋ ስታዲየም የሰው ሰራሽ የሰራር ንጣፉን ከከወነው የታን ኢንጅነሪንግ ባለቤት የቀድሞ ተጫዋች ፉአድ ኢብራሂም ጋር የተደረገ ቆይታ።

አንጋፋው የድሬደዋ ስታዲየም የሰው ሰራሽ ሳር ነጠፋው በዛሬው ዕለት መጠናቀቁን በቀትሩ ዘገባችን መግለፃችን ይታወቃል። የሰው ሰራሽ ሳር ተከላውን ተረክቦ ስራውን ያጠናቀቀው ታን ኢንጅነሪንግ ሲሆን ይህንን ተቋም በባለቤትነት የሚመሩት ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፉአድ ኢብራሂም አጠቃለይ የአርቴፊሻል ሳር ተከላውን ሂደት እና በቀጣይ ሊሰሩ በታሰቡ ስራዎች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

ይህንን ስታዲየም ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ነው የነበረው ሂደት ?

“ስታዲየሙን ከጀመርነው ጊዜ ጀምሮ ወደ ስድስት ወር አካባቢ ነው። አሁን በዚህ በፊፋ ስታንዳርድ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነ አንዳንድ ችግሮች ባጋጠሙን ምክንያት ነው ትንሽ የቆየው እንጂ ፕላናችን በአራት ወር ውስጥ ለመጨረስ ነው ፤ አንዳንድ ማቴሪያል ከውጪ የሚመጡ በዛውም እዚህ ውስጥ መካተት አለባቸው የሚባሉትን በማጣት ምክንያት ትንሽ ወደኋላ ወደ ስድስት ወር ወሰደው እንጂ በፕላናችን መሠረት በአራት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ነበር ግን መጨረሻ ላይ አላሀምዱሊላህ በዚህ መልኩ አልቆ የፊፋ ሰዎችም ነገ ከእንግሊዝ ይመጣሉ። መጥተው ቴስት ያደርጋሉ ፤ ከዛ ከአንድ ሁለት ሳምንት በኋላ ሰርቲፋይ የሆነበትን ሰርተፊኬት የሚሰጡበት ጊዜ ይኖራል።”

በአኛ ሀገር ያሉ አርቴፊሻል መጫወቻዎች በብዙሀኑ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም ይህ የድሬዳዋ ሜዳ ላይ ያለው ሰው ሰራሽ ሳር ከሌሎቹ የተለየ የሚያደርገው ኳሊቲ ምንድነው ?

“ቴስት ይደረጋል እዚህ ሜዳ ላይ የሚገባው ነገር ሁሉ ቴስት ተደርጎ ነው። አርቴፊሻል ሳር በስነ ስርዓት መሰራት ይፈልጋል። ከዛ ውጪ የምትጠቀመው ማቴሪያሎች ኳሊቲ ብቃትን ያለፉ የተረጋገጡ ዕቃዎች መሆን አለባቸው እንጂ አርቴፊሻል በአሁን ጊዜ በዓለም ደረጃ ከተፈጥሮ ሳር በበለጠ የሚሰራው አርቴፊሻል ነው ግን በሀገራችን ሲሰራ በጥሩ ሁኔታ ስላልተሰሩ በሰው ላይ መጥፎ አመለካከትን አሳደረ እንጂ አርቴፊሻል መጥፎ አይደለም። በኢትዮጵያ በፊፋ ደረጃ በሰው ሰራሽ ሜዳ ብቸኛ ነው። ካፍም ፊፋ ያፀደቀውን ነው የሚቀበለው ስለዚህ አርቴፊሻል በኳቲሊ በስነ ስርዓት የተሰራ ነው። ነገ መጥተውም ሲፈትሹ ከዛም ሲያፀድቁ በሀገራቸን ላለው የሜዳ ችግርን መቅረፍ ይችላል በሚል ዕምነት ነው በዚህ ደረጃ የሰራነው።”

በክለብም በብሔራዊ ቡድንም ተጫውተህ አሳልፈሀል እና የእግር ኳስ ተጫዋቾች መሠረታዊ ችግር ከጉዳት ጋር ተያይዞ የሜዳ በጥራት አለመሰራት ነውና ሜደው ጉዳትን ሊቀንስ በሚችል መልኩ እንዲሰራ ምን ተደርጓል ?

“እኔ በአብዛኛው ውጪ ሀገር ነው ያደኩት ፤ ውጪ ሀገርም ብዙ ተጫውቼ አሳልፌ ከዛ በኋላም ለብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ወደዚህ ስመጣ ለድሬዳዋ ከነማም ተጫውቻለሁ። በዛ ጊዜ በሜዳ ችግር ምን ያህል እኔ እንደተቸገርኩ ከተጫዋቾቹ በላይ እኔ እረዳለሁ ብዙ ጥሩ ቦታ ላይ ተጫውቼ ስለመጣው እዚህ ስመጣ አብዛኛው ተጫዋች ኳስ መሬት ላይ ነው የሚፈልገው መሬቱ ጥሩ ስላልሆነ እኔ ብዙ ጊዜ ኳሱን ከፍ አድርጋችሁ ስጡኝ ነው የምለው። ቢያንስ ኳሱ ከፍ ካለ የእኔ ችሎታ ነው የሚወስነው ኳሱን በስነ ስርዓት ኮንትሮል የማድረጉ ግን መሬት ላይ ሲመጣ የሆነ ነገር ይነካው እና አቅጣጫውን ይቀይርብሀል እዛ ላይ ነው በጣም የተቸገርኩት ኳስ ካቆምኩም በኋላ ስፔስፊክሊ በዚህ ተምሬ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ችግርም ስለተረዳሁ ሀገራችን ላይ አሁን አንድ ጥሩ የምትለው ሜዳ የለም ስለዚህ ይሄ ሜዳ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ፣ ለብሔራዊ ቡድንም በጣም ትልቅ ለውጥ የሚያገኙበት ዕድል ነው። ይሄ ነገር ደግሞ መብዛት ነው ያለበት ድሬዳዋ ብቻም ሳይሆን በዚህ ደረጃ ሀገራችን መስራት ትችላለች ስለዚህ መስራት ካልቀረ ኳሊቲን የጠበቀ በፊፋ ተቀባይ በሚደረግ መሰራት ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ።”


የድሬዳዋ ስታዲየምን አጠናቃችኋል ቀጣይ የታን ኢንጂነሪንግ ቀጣይ ጉዞ ምንድነው? ዕቅዱስ?

“ታን ኢንጂነሪንግ ይሄንን ስራውን ማስፋፋት ነው። በዕርግጥ አንዳንድ ስራዎችን ወስደን እየሰራን ያለናቸው ስራዎች አሉ ድሬዳዋ ላይ ይሄ ሁለተኛ ሜዳችን ነው ሦስተኛ ሜዳ ወስደን እየሰራን ነው ለዛውም በቅርቡ ጎዴ ላይ እንጀምራለን ሱማሌ ክልል ማለት ነው እንደውም እነርሱ ወደ ሦስት የተለያየ አይነት ፕሮጀክት ነው ጎዴ ፣ ሀገሀቡር እና ቀብሪደሀር ላይ የመስራት ፍላጎት አላቸው በቅርቡ እዛ ነበርኩ በቅርቡ እንጀምራለን ታን ኢንጂነሪንግ ስፔሲፋይ ያደረግነው በስፖርት ፋሲሊቲ ነው ትልቁም በሀገራችን ችግር ላይ ያለው ይሄ ስለሆነ በበለጠ የምረዳውም ነው እኔ ተጫውቼ ያለፍኩበት ሁሉን ነገር ያየሁበት ስለሆነ እንደተማርኩት ሙያ ሳይሆን በተፈጥሮ ስለማውቀው በዚህ በምናውቀው ስራ ላይ ኢፌክቲቭ ሆነን ለመስራት በደንብ ማወቁ ስለሚያስፈልግ ታን ይሄንን በደንብ አስፋፍቶ እዚህ ድሬዳዋ ብቻም ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ስራውን አስፋፍቶ ለመስራት ዝግጁ ነው።”

ሜዳዎች ከተሰሩ በኋላ ከእንክብካቤ ጉድለት ይጎዳሉ ይሄ ሜዳ ይህ ችግር እንዳይገጥመው ተቋሙ ምን አስቧል?

“ተቋሙ በዚህ ብዙ ገንዘብ አውጥቶ ነው የሰራው ይሄን ሜዳ። መጀመሪያም ሲወስን ኳሊቲ ያለው በፊፋ ስታንዳርድ አፕሩቭ የሚያደርገውን እንሰራለን ብሎ ነበር አቋም ይዞ ዕቅድ ያወጣው ሜዳው ሲያልቅ እንደሚንከባከቡት እግር እንዳይበዛበት እንደሚጠበቅ አንዳንድ ጠጋኞችም እንደሚያስፈልጉ እኔም መመሪያ በመስጠት ይሄ ሜዳ ሳይበላሽ ረጅም ጊዜ እንዲቆይ የእነርሱም ትልቅ ፍላጎት ስለሆነ በደንብ ይጠበቃል። ለፕሪምየር ሊግም ይሁን ለብሔራዊ ቡድንም ጥሩ ዕድል ስለሆነ በደንብ ይጠበቃል።”