የአሥራ ሦስተኛ ሣምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።
ግብ ጠባቂ
በረከት አማረ – ኢትዮጵያ ቡና
ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ኢትዮጵያ መድን ላይ ባሳካበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግብ ጠባቂው በረከት አማረ የመድንን በተለይ ከርቀት ይደረጉ የነበሩ ሙከራዎችን በማክሸፍ እና የግብ ክልሉን በንቃት ይጠብቅበት ከነበረው መንገድ በመነሳት በምርጥ ስብስባችን ውስጥ በቋሚዎቹ መካከል መርጠነዋል።
ፍቅሩ ዓለማየሁ – አዳማ ከተማ
በአዳማ ከተማ መለያ በሁሉም የሊግ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት በመሰለፍ የኋላ መስመሩ ላይ ወደር የለሽ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ፍቅሩ ቡድኑ ባህርዳርን 2ለ1 በረታበት ጨዋታ ላይም ካደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር ላገኙት የፍጹም ቅጣት ምትም ቁልፍ ምክንያት ነበር።
ኢስማኤል አብዱልጋኒዩ – ድሬዳዋ ከተማ
ብርቱካናማዎቹ ከሀዲያ ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ የመሃል ተከላካዩ ብቃት የሚደነቅ ነበር። በተለይም በርካታ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ከማሸነፉም በላይ ጊዜያቸውን በጠበቁ ሸርተቴዎች ሲያቋርጣቸው የነበሩ ኳሶች እጅግ አስደናቂ ነበሩ።
ፍሪምፓንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈረሰኞቹ ከሽንፈት መልስ ወደ ድል በተመለሱበት ወሳኙ የንግድ ባንክ ጨዋታ ተከላካዩ የንግድ ባንክን ፈጣን አጥቂዎችን በማቆም እንዲሁም የአየር ላይ ኳሶች ወደ አደጋነት እንዳይለወጡ ከማድረግም በተጨማሪ የቡድኑን ሁለተኛ ጎልንም ከቅጣት ምት አስቆጥሯል።
በፍቃዱ ዓለማየሁ – ኢትዮጵያ ቡና
ቡናማዎቹ በድል በተወጡት የኢትዮጵያ መድን ጨዋታ በፍቃዱ ዓለማየሁ ሌላው የቡድኑ ልዩነት ፈጣሪው ተጫዋች ነበር። አንተነህ ተፈራ በጨዋታው ሦስት ጎሎችን ከመረብ ሲያዋህድ ተጫዋቹ የመጀመሪያዋ ጎል እንድትቆጠር አመቻችቶ ማቀበልም ችሏል።
አማካዮች
ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጥሩ ምሽትን ባሳለፉበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ጨዋታ ናትናኤል ዘለቀ ሚናው የገዘፈ ነበር። መሐል ሜዳውን በመቆጣጠርም ሆነ የቡድኑን የመከላከል ሚዛን በመጠበቅ የተዋጣለት የነበረው ናትናኤል ለቡድኑ የመጀመሪያ ግብም በድንቅ ሁኔታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
አበባየሁ ሀጂሶ – ወላይታ ድቻ
ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ለሚያደርገው ወላይታ ድቻ የአበባየሁ ሚና ጎላ ያለ ነው። በተለይ ቡድኑ ሀምበርቾን በረታበት ጨዋታ አማካዩ ያሳየው እንቅስቃሴ ቡድኑን እጅግ ጠቅሟል። ከተከላካይ እየተቀበለ የሚያሰራጫቸው ኳሶች ፣ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን የሚያስጀምረበት ሂደት ተጫዋቹን የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።
ሽመልስ በቀለ – መቻል
ከጨዋታ ጨዋታ እየደመቀ የሚገኘው አንጋፋው አማካይ በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ላይ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለቡድኑ ከማድረግ ባለፈ አሸናፊ ያደረጋቸውን ሁለተኛ ግብ እንዲቆጠር ከቅጣት ምት በማሻማት በሲዳማ ተጫዋች በራሱ ላይ እንዲያስቆጥር ያደረገበት ሂደት ድንቅ ነበር።
አጥቂዎች
ዓሊ ሱሌማን – ሀዋሳ ከተማ
ሀዋሳ ከተማ ወደ ድል በተመለሱበት ወሳኙ የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ካሳዩት ተጫዋቾች አንዱ ዓሊ ሱሌማን ነው። በጨዋታው አንድ ጎል ያስቆጠረው ፈጣኑ አጥቂ ዓሊ በርካታ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት ጨዋታ በግሉ ያሳየው ብቃት እና ታታሪነት የሚደነቅ ነበር። በዚህ መነሻነት የሳምንቱ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ሊካተት ችሏል።
ቦና ዓሊ – አዳማ ከተማ
አዳማዎች ባህርዳር ከተማን 2ለ1 በመርታት ተከታታይ ድል ሲያሳኩ የአጥቂው እንቅስቃሴ ግሩም ነበር። በተለይም የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ ከመረበሹ ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያ ግብም ከሳጥን ውጪ ማስቆጠር ችሏል።
አንተነህ ተፈራ – ኢትዮጵያ ቡና
ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ነጥቦችን ወደ ካዝናው በከተተበት የመድኑ ጨዋታ አንተነህ ተፈራ ቀኑ ነበር ማለት ይቻላል። በ12ኛው ሳምንት ብቸኛ የማሸነፊያ ግብን አስቆጥሮ የነበረው ወጣቱ አጥቂ በመድኑ ጨዋታም ሦስት ጎሎችን ለቡድኑ በማስቆጠር በተከታታይ ጨዋታ ወሳኝነቱን አስመስክሯል።
አሰልጣኝ – ዘሪሁን ሸንገታ
በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሦስት ጎል ልዩነት ሲረታ ቡድኑ ያሳየው ብቃት ልዩ ነበር። በአሠልጣኝ ዘሪሁን የሚመራው ቡድኑ ከአስከፊው የድሬዳዋ ሽንፈት በብቃትም በውጤትም ያገገመበት መንገድ እንዲሁም የተጋጣሚው ንግድ ባንክን ጠንካራ ጎን ያከሸፉበት እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር። ይህንን ተከትሎም አሠልጣኝ ዘሪሁንን የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን አሰልጣኝ እንድናደርጋቸው አስችሏል።
ተጠባባቂዎች
አብዩ ካሳዬ – ድሬዳዋ ከተማ
ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና
ፍጹም ፍትሕዓለው – ባህር ዳር ከተማ
ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ
ቢኒያም በላይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና
ቢኒያም ፍቅሩ – ወላይታ ድቻ
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ፋሲል ከነማ
ጌታነህ ከበደ – ፋሲል ከነማ