ሪፖርት | ቡናማዎቹ መቻልን ረምርመውታል

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር በግብ ተንበሽብሸው መቻልን 4ለ0 ረተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር መቻል እና ኢትዮጵያ ቡና ሲገናኙ መቻሎች በ13ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡናን 2ለ1 ከረቱበት አሰላለፍ ምንተስኖት አዳነን አሳርፈው ግሩም ሀጎስን ሲተኩ ቡናማዎቹም በተመሳሳይ ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን በአንተነህ ተፈራ ሦስት ግቦች 3ለ0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በመጨረሻው ልምምድ ወቅት ጉዳት በገጠመው ጫላ ተሺታ ምትክ ኪያር መሐመድን ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

12፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቡናማዎቹ 2ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን አደገኛ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ አንተነህ ተፈራ ግብ ጠባቂውን አልዌንዚ ናፊያንን በማለፍ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ቢገባም ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ተከላካዮቹ አግደውበታል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን በመድረስ መታተራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ 7ኛው ደቂቃ ላይ በአማኑኤል አድማሱ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርገው በግቡ የቀኝ ቋሚ ለጥቂት ሲወጣባቸው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አብዱልከሪም ወርቁ ከዋሳዋ ጄኦፍሪ ጋር በመሆን ከዳዊት ማሞ የነጠቀውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት ገብቶ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ኳሱን ያገኘው መስፍን ታፈሰ አስቆጥሮታል።

ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት የተቸገሩት መቻሎች በአጋማሹ የተሻለውን ለግብ የቀረበ  ሙከራቸውን 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዳዊት ማሞ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ በረከት አማረ ሲመልሰው የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ተከላካዩ ስቴፈን ባዱ አኖርኬም ከፍ አድርጎ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በድጋሚ አስወጥቶበታል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች አይበገሬ ሆነው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች 30ኛው ደቂቃ ላይም በዚሁ እንቅስቃሴ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። አማኑኤል አድማሱ ከራሱ የሜዳ ክፍል ያሻገረለትን ኳስ የተቆጣጠረው አብዱልከሪም ወርቁ ኳሱን እየገፋ በመውሰድ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ድል ካደረጉ የመጀመሪያውን ዙር መሪነታቸውን የሚያረጋግጡት መቻሎች ከወትሮው በተለየ ቀዝቃዛ በሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሰብረው ለመግባት ሲቸገሩ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከመጀመሪያው በተመሳሳይ ከቆመ ኳስ የተሻለ ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም ምንይሉ ወንድሙ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መቻሎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ለመያዝ እና ተጭነው በመጫወት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የተሳካላቸው የአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ ተጫዋቾች 51ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው በመልሶ ማጥቃት የወሰዱትን ኳስ አማኑኤል አድማሱ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው አብዱልከሪም ወርቁ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ለተመልካች ሳቢ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ተጫዋቾች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ቢታተሩም በ59ኛው ደቂቃ ልፋታቸው ላይ ውሃ የቸለሰ አጋጣሚ ተፈጥሮባቸዋል። ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ከአስቻለው ታመነ በተቀበለው ኳስ ለማታለል ሲሞክር በሠራው ስህተት ኳሱን ያገኘው አንተነህ ተፈራ በቀላሉ ግብ አድርጎታል።

በቀጣይ ደቂቃዎች ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት የጠሩ የግብ ዕድሎች ግን አልተፈጠሩም ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ ቡናዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። አብዱልከሪም ወርቁ በድንቅ ዕይታ የሰነጠቀለትን ኳስ የመቻል ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ብለው በተዘናጉበት ቅጽበት ሾልኮ በመውጣት ያገኘው ተቀይሮ የገባው መሐመድኑር ናስር ግብ ጠባቂውን አልዌንዚ ናፊያንን በማለፍ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ 90+1ኛው ደቂቃ ላይ በመቻል በኩል ተቀይሮ የገባው ቺጂኦኬ ናምዲ አኩኔቶ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ቡናማዎቹ በመልሶ ማጥቃት ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው መሐመድኑር ናስር ለመስፍን ታፈሰ ለማቀበል ሲሞክር ኳሱ ረዝሞበት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ከጨዋታዉ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በሁሉም መልክ ጥሩ እንዳልነበሩ በመጠቆም መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ የወሰዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ በመሆናቸው ድሉ እንደሚገባቸው ሲናገሩ  መሸነፋቸው ለረጅም ጊዜ ዝግጅት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ በበኩላቸው ጥሩ ጨዋታ እንደነበር እና የተጫዋቾቻቸው በራስ መተማመን እየተጠናከረ እንደመጣ ሲጠቁሙ ከድሉ ባሻገር ግብ አለማስተናገዳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።