ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የጀመረው 14ኛ ሳምንት ነገም ሲቀጥል በነገው ዕለት የሚካሄዱትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባህር ዳር ከተማ
ከተከታታይ የአቻና የሽንፈት ውጤቶች በኋላ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።
አዳማ ከተማን አንድ ለባዶ ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ተከታታይ አራት ጨዋታዎች አቻ የተለያዩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከሳምንታት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የጣና ሞገዶቹን ይገጥማሉ። ሀድያዎች በሊጉ ከፍተኛውን የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል። ቡድኑ ከሌላው በርካታ የአቻ ውጤት ካስመዘገበው አዳማ ከተማ በሦስት ጨዋታዎች ልቆ በውድድር ዓመቱ በዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በነገው ጨዋታም ከተከታታይ የአቻ ውጤት ለመላቀቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሀድያዎች ድሬዳዋ ከተማን ከገጠሙበት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ጨምሮ ባደረጓቸው የቅርብ ሳምንት ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻሎች ቢያሳዩም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የግብ ማስቆጠር ችግር ይታይባቸዋል። አሰልጣኝ ግርማ በመከላከሉ ረገድ የሠሩትን ጥሩ ጥምረት በፊት መስመሩ ላይ የመድረግ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በታች ማስመዝገቡ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ድክመቶች እንዳሉ ማሳያ ነው።
ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ባህርዳር ከተማዎች ከሳምንታት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ባለፉት አስራ አንድ ሳምንታት ሽንፈት ካልገጠመው ሀድያ ሆሳዕና ይጫወታሉ። የጣና ሞገዶቹ በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ ተከታታይ የሆነ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ቢችሉም በስምንተኛ ሳምንት ላይ ድሬዳዋ ከተማን ሁለት ለአንድ ካሸነፉበት ጨዋታ ወዲህ ግን ማሸነፍ አልቻሉም።
ቡድኑ ከተጠቀሰው ሳምንት በኋላ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈትና ሁለት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገብ ችሏል። ቡድኑ ከውጤቱም ባሻገር የከዚህ ቀደም ዋነኛ ጥንካሬውን አጥቷል። የጣና ሞገዶቹ በሊጉ አስራ ሰባት ግቦች በማስቆጠር ጥሩ የግብ ማስቆጠር ቁጥር ማስመዝገብ ችለው ነበር። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ግን ሁለት ግቦች ብቻ አስቆጥረዋል። አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የተጠቀሰው የግብ ማስቆጠር ችግር ቀርፈው ይቀርባሉም ተብሎ ይጠበቃል።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ግርማ በቀለ እና ዳግሞ ንጉሤ በጉዳት በረከት ወልደዮሐንስ ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ አይኖሩም። በጣና ሞገዶቹ በኩል ማሊያዊው አጥቂ ሱሌይማን ትራኦሬ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ብቸኛ ተጫዋች ነው።
ጨዋታውን ሔኖክ አበበ በመሐል ዳኝነት ፣ ሲራጅ ኑርበገን እና ዘመኑ ሲሳይነው በረዳትነት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን በጋራ ይመሩታል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ስድስት ጊዜ ተገናኝተው እኩል ሦስት ጊዜ ተሸናንፈዋል። የጣና ሞገዶቹ አምስት ፣ ነብሮቹ ደግሞ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ሀምበርቾ
ሀዋሳ ከተማና ሀምበርቾ የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።
ከተከታታይ አምስት ሽንፈቶች አገግመው በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች በአስራ አምስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ኃይቆቹ በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች ከማገገሙም ባለፈ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ላይም በጎ ለውጦችን አምጥቷል። በዓሊ ሱሌይማን የሚመራው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነው። ሀዋሳዎች በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከነማ ላይ ካስቆጠሯቸው ሦስት ግቦች ወዲህ ለዘጠኝ ሳምንታት በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ሳያስቆጥሩ ዘልቀው ነበር። አሁን ግን በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግብ በማስቆጠር ይህንን መጥፎ ክብረ ወሰን ማሻሻል ችለዋል። ባለፉት ጨዋታዎች ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የማይሰጥና መልሶ ማጥቃት ላይ ያተኮረ አቀራረብ የነበራቸው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የነገው ተጋጣሚያቸው መከላከል ላይ ያተኮረ ጠጣር አጨዋወት ኳሱን እንዲቆጣጠሩ ሊያስገድዳቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል። በተጋጣሚ የግብ ክልል ሰፊ የመጫወቻ ክፍል ቦታ ያገኛሉ ተብሎ ስለማይጠበቅም ከተለመደው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የተለየ አቀራረብ ይዘው የሚቀርቡበት ዕድል የሰፋ ነው።
በታሪካቸው የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ድል ካገኙ በኋላ በመጨረሻው ሳምንት በወላይታ ድቻ የአንድ ለባዶ ሽንፈት አስተናግደው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ሀምበርቾዎች በስድስት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ይገኛሉ። ሀምበርቾዎች በውጤት ረገድ በአንጻራዊነት መጠነኛ መሻሻል አሳይተው ከቀደመው ተከታታይና ድል አልባ ጉዞ የተሻለ ጊዜ ማሳለፍ ቢችሉም የወጥነት ችግር ይታይባቸዋል። ቡድኑ ቢያንስ በመጀመሪያው ዙር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቦ ለማጠናቀቅም የተጠቀሰውን ችግር መቅረፍ ይጠበቅበታል። በመጠኑ ወደ መከላከሉ ያደላ አጨዋወትን የመረጡት ሀምበርቾዎች በተለይም ከባህርዳር ከተማና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኘው ሲዳማ ቡና ጋር ባደረጓቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ያሳዩት እንቅስቃሴ ቡድኑ መሻሻሎች እንዳሉት ማሳያዎች ናቸው። ሆኖም በአስር ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን የመቀየር ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በውድድር ዓመቱ ስድስት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በጋራ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ ቡድን ነው።
ሀዋሳዎች በቅጣት ምክንያት ጨዋታው ከሚያልፈው አቤኔዘር ዮሐንስ ውጭ የሚያጡት ተጫዋች የለም። ሀምበርቾዎችም በተመሳሳይ የቴዎድሮስ በቀለን አገልግሎት አያገኙም።
ለጨዋታው መስፍን ዳኜ በዋና ዳኝነት ፣ ደረጄ አመራ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም በረዳትነት ሃይማኖት አዳነ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙበት ነው።