የግል አስተያየት | የጨዋታ ነጻነት


በደስታ ታደሠ

በኢትዮጵያ ቡና እና በመቻል መካከል ከተደረገውና በኢትጵያ ቡና 4-0 ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው አማካኝ አብዱልከሪም ወርቁ ስለ ውጤታማነታቸው ተጥይቆ ሲመልስ ‹ በአሰልጣኙ የተሰጠን የመጫወት ነፃነት › ብሎ ሲመልስ ሰማሁት፡፡ እርግጥ ነው አንድ ቡድን በተጋጣሚው ላይ የበላይ ለመሆን የመጫወት ነፃነት መኖሩ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ እግር ኳስ ከፍተኛ ዝግጀት የሚፈልግ እንደመሆኑ በቴክኒክ፣ በታክቲክ፣ በአካል ብቃት እና በስነልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል። በተጨማሪም በማጥቃት፣ ከማጥቃት ወደ መከላከል ባለ ሽግግር፣ በመከላከል እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት ባለ ሽግግር እንዲሁም በመከላከል ላይ ጠንክሮና አዘወትሮ መስራት ይሻል፡፡ በተጨማሪም የጨዋታ ሞዴላችን (ዘይቤያችን) ላይም ትኩርት መስጠትን ግድ ይላል፡፡

በተለይም ተጫዋቾች በጫና እና ድካም ውስጥ ሲሆኑ ውሳኔ የመስጠት ብቃታቸው እንዲያድግ በጨዋታ ላይ ውሳኔዎችን በራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በየትኛውም የጨዋታ ሁኔታ ውስጥ ጥሩ ውሳኔ መስጠትን መለማመድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም በጨዋታዎች ላይ ውጤት ለማምጣት ሁነኛ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ኳስን ማጣት ወይም መነጠቅ የደካማ ቴክኒካዊ ክህሎት ውጤት ብቻ ሳይሆን የመጥፎ ውሳኔም ክትያ (Consequence) ነው፡፡ የተጫዋቾች ትክክለኛ ውሳኔዎችን በተገቢው ጊዜና ቦታ የመወሰን ብቃት ደግሞ በጨዋታ ላይ በሚኖር ነፃነት ብቻ ሳይሆን በልምምድ ላይም ጭምር ያድጋል ፡፡ ባላፉት ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ያልተሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ላይ ይህ ያለ አሉታዊ ጫና የመጫወት እና ውሳኔዎችን የመወሰን ነፃነት ይንፀባረቅበታል፡፡
እግር ኳስ በትልቅ ሜዳ 11 ለ 11 የሚደረግ ጨዋታ ነው ፡፡ ከዚህም በላይ በእግር ብቻ የሚደረግ ጨዋታ መሆኑ የሚታወቅ ነው ፡፡ስለዚህም ኳስን አንድ ቡድን ብቻ ይዞ የሚቆይበት ምንም ዋስትና የለም ፡፡ይህ ማለት እግር ኳስ በጣም ውስብስብ እና ያልተገመቱ ድርጊቶች የሚከሰቱበት ስፓርት ነው ፡፡ እንደ ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ሬይመንድ ቨርሂን እይታ ከእነዚህ ባህሪያት የተነሳ እግር ኳስ አሰልጣኙ በመስመር ላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው ነገር አይደለም ፡፡በጨዋታ ሰዓት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ውሳኔዎችን የመወሰን ሃላፊነት ያለባቸው ተጫዋቾች ናቸው ፡፡ስለዚህ ከውሳኔ አሰጣጥ አንፃር እግር ኳስ የተጫዋቾች ጨዋታ ነው፡፡
ይህ የውሳኔ አሰጣጥ ነፃነት እና ችግሮችን የመፍታት ልማድ ታዳጊዎች ከልጅነት ጀምሮ ሊያዳብሩት የሚገባ ነው ፡፡በሃገራችን እግር ኳስ የታዳጊዎች ስልጠና ላይ አሰልጣኞች ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፣ ችግሮችን የመፍታት እና ውሳኔዎቻቸውን የመቆጣጠር ልማድ ከፍተኛ ነው ፡፡ በአሰልጣኝ የበዙና ተደጋጋሚ ትዕዛዛት የተሞሉ፣ አሰልጣኞች ቆመው የሚሰሩ ልምምዶች በርካታ መሆናቸው እና በጨዋታ ቀንም አሰልጣኞች በሜዳው ዳር ሆነው የማያቋርጥ ትዕዛዞችን መስጠታቸው ተጫዋቾቻን ይህንን ክህሎት ሳያዳብሩ እንዲያድጉ እያደረገ ነው፡፡ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ የታዳጊ ማሰልጠኛዎች መብዛታቸው እንደ በጎ የሚነሳ ጉዳይ ቢሆንም በዛው ልክ ደግሞ ልምምዶቹ በጣም ቁጥጥር የበዛባቸው መሆናቸው የታዳጊዎቻችን በጨዋታ ላይ ውሳኔ የመስጠት አቅማቸው የተገደበ እንዲሆን አድርጓል፡፡
ታዳጊ ተጫዋቾቻን እንዴት ሊያስቡ እንደሚገባ መማር ይኖርባቸዋል፡፡ በጨዋታ ቀን ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ በልምምድ ሜዳ ላይ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ የስልጠና ከባቢዎችን ማመቻቸት እና ይህንን ሊያሳድጉ የሚችሉ የስልጠና መንገዶችን መከተል ያስፈልጋል ፡፡ ተግዳሮቶች ሲገጥሟቸው እና ችግሮችን የመፍታት ግዴታ ውስጥ ሲገቡ በተሻለ እና በፈጣን መንገድ እንዲያድጉ ይረዳቸዋል፡፡ በጨዋታ ላይ የሚከሰተው ነገር ይህ ነው፡፡

ለተጫዋቾቸን የመማር ነፃነት ልንሰጣቸው ይገባል ፡፡ውሳኔ ለመስጠት እና ሃላፊነት ለመውሰድ አሰልጣኙ በሚያስቀምጠው ታክቲካዊ መዋቅር እና በቡድኑ የጨዋታ ዘይቤ ውስጥ ነፃነት ማግኘት አለባቸው ፡፡እግር ኳስ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ውሳኔ የሚሰጥበት ጨዋታ እንደመሆኑ የአእምሮ ፍጥነት አስፈላጊ ነው፡፡ የላቁ ተጫዋቾችን ከመካከለኛ ተጫዋቾች የሚለየው ዋነኛ ነገር የአእምሮ ልህቀት ነው፡፡ ስፔናዊዎቹን ዣቪ፣ኢኒየስታ፣ ቡስኬትስ፣ ዳቪድ ሲልቫ ወይም ዣቪ አሎንሶን እንዲሁም ፓርቱጋላዊው በርናርዶ ሲልቫን እንደ ምሳሌ ብንመለከት አንዳቸውም የገዘፈ ቁመና ወይም በከፍተኛ ጉልበት ወደ ላይ የመዝለል ወይም የመስፈንጠር ልዩ ችሎታ (explosive power) የላቸውም ፡፡ነገር ግን ሚናቸውን በመወጣት በጣም ግሩም ናቸው ፡፡ጨዋታን በማንበብ፣ዙሪያቸውን በመቃኘት ፣ተቃራኒ ቡድን ቀጥሎ ምን ሊሰራ እንደሚችል ቀድሞ በማሰብ፣ በፍጥነት ትክክለኛ ውሳኔ በመወሰን ጎበዞች ናቸው፡፡ የኛ ሃገር ተጫዋቾች እንዲህ ወዳለው ዓይነት ብቃት እንዴት መምጣት ይችላሉ? የሚለውን በጥልቀት ማሳብ በጣም ጠቃሚ ነው ፡፡ በሜዳ ላይ የሚያጋጥሙ በተለይም ከተጋጣሚ ቡድን አጨዋወት አንፃር የሚመጡ ችግሮችን በመፍታት የላቁ እንዲሆኑ ከቡድኑ የጨዋታ ዘይቤ እና ታክቲካዊ መዋቅር ሳይወጡ በፍፁም ነፃነት ልናሳድጋቸው ይገባል፡፡

‹‹ በጨዋታ ያጋጠሙኝ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ከእኔ በፍጥነት የተሻሉ እና ጠንካራ ናቸው ፡፡አካላዊ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው ውሳኔ አሰጣጣችን ነው፡፡የአንዳንድ ተጫዋቾች ከፍተኛው የአእምሮ ፍጥነት 80 ይሆናል፡፡ ሌሎች ደግሞ እስከ 200 የመደረስ አቅም አላቸው። ሁልጊዜም 200 ላይ ለመድረስ እጥራለሁ።››ዣቪ ሄርናዴዝ
እግር ኳስ ከዚህ በላይ ፈጣን እየሆነ እንደሚሄድ እና የተጫዋቾች የቴክኒክ ደረጃም በከፍተኛ ሁኔታ እያደደገ እንደሚመጣ እንዲሁም ከፍተኛ ጫና ያላቸው ጥረቶች በጣም ወሳኝ እየሆኑ እንደሚሄዱ አያጠያይቅም፡፡ቡድኖች በጣም ተጠጋግተው መጫወታቸው ሊገኝ የሚችለውን ከፍት ቦታ ይቀንሳል ፡፡በዚህም በቀጣይ ዘመን እግር ኳስ ላይ የአእምሮ ፍጥነት እና ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚኖራቸው ነፃነት ከዚህም በላይ አስፈላጊ እየሆነ ይሄዳል፡፡

ያለክርክር የዓለም ምርጥ ተጫዋች የሆነው ሊዮኔል ሜሲ እንደሚለው በዘመናዊ እግር ኳስ በአብዛኛው ለማሰብ ቦታ የለም ፡፡አብዛኞቹ ድርጊቶች በደመነፍስ የሚከወኑ ናቸው ፡፡በዚህ ደረጃ ተጫዋቾች ብቁ እንዲሆኑ ተጫዋቾች በታዳጊ እና በወጣትነታቸው በልምምድ ሜዳ ላይ እና ከዚያም ውጪ ከኳስ ጋር ብዙ ማሳለፍ እና ውሳኔ አሰጣጥ ብቃታቸውን ሊያሳድግ በሚችል ከባቢ ማደግ ይገባቸዋል፡፡የላቁት ተጫዋቾች ብቃታቸውን ወደ ፍፁምነት ለማስጠጋት በታዳጊነታቸው ከመደበኛው ልምምድ ውጪ ከጓደኞቻቸው ጋር በመጫወት ያሳልፋሉ፡፡ይህም ተደጋጋሚ የአሰልጣኝ ትእዛዝ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ በድፍረት በጨዋታ ላይ ውሳኔ የመወሰን ብቃትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፡፡

ሜሱት ኦዚል የተለየውን ብቃቱን ለማሳደግ በዕድሜ ከሚበልጡት ልጆች ጋር ‹‹the cage›› ተብሎ በሚጠራ ሜዳ ውስጥ ከትምህርት መልስ ይጫወት ነበር፡፡‹‹the cage›› የሚባለው ሜዳ በኮንክሪት የሚሰራ እና ዙሪያውን በሽቦ የታጠረ ሜዳ ነው፡፡ ኔይማር ከፉትሳል ጨዋታ ብዙ እንዳተረፈ ይናገራል፡፡ሮናልዲኒሆ የተለዩ ተስጦዎቹን ድፍረት የሞላበት ልዩ ክህሎቱን ከአሸዋ ላይ ጨዋታ አዳብሯል ፡፡ኢብራሂሞቪች በታዳጊነቱ የመንገድ ላይ የትንሽ ሜዳ ጨዋታ አብዝቶ ተጫውቷል፡፡ቲየሪ ሄነሪ በመኪና ማቆሚያዊች ስፍር በመጨዋት ብዙ ሰዓት አሳልፏል፡፡ይህም ከፍ ባለው የአውሮፓ ሊጎች ላይ በነፃነት እንደልባቸው ሲፈነጩ ማየት አስችሎናል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በንፅፅር ኢትዮጵያ ቡና የተመልካችን ቀለብ የሚይዝ ጨዋታ ይጫወታል፡፡ይህም ቡድኑ የሚከተለው የጨዋታ ዘይቤ እንደለ ሆኖ ተጫዋቾች በተወሰነ መንገድ ያላቸው የጨዋታ ላይ ነፃነት እንደጠቀማቸው በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል፡፡ይህ በተቻለ መጠን በሁሉም ክለቦቻችን ሊለመድ የሚገባ ነገር ነው ፡፡አሰልጣኞች ተጫዋቾች ቡድኑ ከሚጠቀመው ታክቲካዊ መዋቅር ሳይወጡ እራሳቸውን እንዲገልጡ እና እምቅ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ሊረዱዋቸው ይገባል፡፡ ታዳጊ ተጫዋቾቻን ላይ በዚህ መንገድ ብንሰራ ደግሞ አሁን ከሉን የላቁ ተጫዋቾችን እንደናፈራ ያደርጋል፡፡

ስለ ፀሐፊው

ጸሀፊው አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ይባላል። አሰልጣኙ በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ለአስር ዓመታት ያህል አሰልጥኗል፡፡ የአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑን በአሰልጣኝነት መርቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም የእግርኳስ መሠረታውያን ላይ ጥልቅ አስተያየቱን በመጻፍም ይታወቃል