17 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በተደረጉበት ጨዋታ አባካኝ ሆነው ያመሹት ኃይቆቹ ሀምበርቾን 2-0 ረተዋል።
በምሽቱ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ እና ሀምበርቾ ሲገናኙ ኃይቆቹ በ13ኛው ሳምንት ወልቂጤ ከተማን 2ለ1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ በመድኃኔ ብርሃኔ ምትክ እንየው ካሳሁን ተተክቷል። ሀምበርቾዎች በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት በወላይታ ድቻ 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ተመስገን አሰፋ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና ኤፍሬም ዘካርያስ በንጋቱ ጎዴቦ ፣ ማናየ ፋንቱ እና አቤል ከበደ ተክተው በቋሚ አሰላለፍ አስጀምረዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ። የጨዋታው የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድልም 7ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጠር የኃይቆቹ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ከራሱ የግብ ክልል የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ወገን ሆኖ ቢመታውም በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ይዞበታል።
ሀዋሳዎች ዓሊ ሱሌይማንን ትኩረት ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ቢችሉም ፈጣኑ አጥቂ በእርጋታ ማነስ ሲያባክናቸው ተስተውሏል። በተለይም 20ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረው ኳስ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ሲቀር በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ የሀምበርቾው ተመስገን አሰፋ ተጭኖ በቀማው ኳስ ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ሀምበርቾዎች ከኋላ መስመራቸው ላይ በሚተውት ክፍት ቦታ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያስተናግዱ 33ኛው ደቂቃ ላይም ራሱ ዓሊ ሱሌይማን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሆኖም ያለ ማቋረጥ በጥቂት ንክኪዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት ኃይቆቹ 44ኛው ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አዲሱ አቱላ ከግራ መስመር ከሳጥን ውጪ ያደረገውን አስደናቂ ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ሳይዘጋጅ ያገኘው ኢዮብ ዓለማየሁም ሊጠቀምበት አልቻለም።
በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ፉክክር ያድርጉ እንጂ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ሀምበርቾዎች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው አፍቅሮተ ሰለሞን ከአልዓዛር አድማሱ በተቀበለው ኳስ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ አድኖበታል።
ከዕረፍት መልስ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፍጹም ብልጫ በመውሰድ ተጭነው የተጫወቱት ኃይቆቹ የመስመር አጥቂ ኢዮብ ዓለማየሁ በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረው ኳስ በኤፍሬም ዘካሪያስ ተጨርፎ ሊቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የሀምበርቾው አማካይ በፍቃዱ አስረሳኸኝ ከመስመር መልሶታል።
ጨዋታው 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያውን ግብ አስመልክቶናል ፤ የሀዋሳዎች ዋነኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የሆነው ዓሊ ሱሌይማን ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በግቡ የቀኝ ክፍል በኩል መረቡ ላይ አርፏል።
ኃይቆቹ በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው እዮብ ዓለማየሁ ከዓሊ ሱሌይማን በተቀበለው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ሙከራውን ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ በእግሩ አግዶበታል።
የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት የተቸገሩት ሀምበርቾዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም ዘካሪያሰ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ የተሻለ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግን ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ እጅግ ተቃርበው ነበር ፤ ታፈሰ ሰለሞን በድንቅ ዕይታ በሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው እዮብ ዓለማየሁ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማንም ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርጎ ወርቃማው የግብ ዕድል አባክኗል።
የሀዋሳ ከተማ አባካኝነት በተደጋጋሚ ጎልቶ እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሀምበርቾዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በተሻለ እንቅስቃሴ መታተር ቢችሉም ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ የሀምበርቾው አፍቅሮተ ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳያስመለክተን ሊጠናቀቅ ቢቃረብም 90+4ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱሌይማን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ተባረክ ሄፋሞ አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በጨዋታው ምንም እንኳን ሀዋሳዎች የበላይን ቢታይበትም በድምሩ 38 የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተን አዝናኝ ጨዋታ ሆኖ ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው አሰልጣኝ መላኩ ከበደ የሚፈልጉት የጨዋታ ቀመር እስኪሳካ እየሞከሩ እንደሆነ ጠቁመው የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይም ክፍተት እንዳለ አልሸሸጉም በአንፃሩ የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ብዙ ጊዜ ወደ ጎል ቢደርሱም ዕድሎችን አለመጠቀማቸውን ጠቁመው አጥቂ መስመር ላይ አለመረጋጋት እንዳዩ ተናግረዋል። ሁለተኛው ጎል ሲቆጠርም ያሳዩት የደስታ ስሜት ለድሉ የማረጋገጫ ጎል ስለሆነ በዛ ምክንያት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።