መረጃዎች | 56ኛ የጨዋታ ቀን

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ስለሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።


አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው የመጀመሪያው መርሐግብር ተጠባቂ ነው።

ከተከታታይ አምስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች ከነገው ተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው በ6ኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል። አዳማዎች ከባህር ዳር ከተማና ሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች በማስቆጠር ለሳምንታት ዘልቆ የነበረው የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን ፈተዋል። ቡድኑ ከተከታታይ ድሉ በፊት ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ አስቆጥሮ ነበር። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በማጥቃት አጨዋወታቸው በርካታ ለውጦች ያደረጉት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቅያሪዎቹ የቡድኑን የግብ ማስቆጠር ችግር ፈተዋል። በነገው ዕለት ግን በሊጉ ጠንካራ የመከላከል ጥምረት ካላቸው ክለቦች አንዱ ስለሚገጥሙ ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።


በመሪዎች ነጥብ መጣል ምክንያት ልዩነቱን የማጥበብ ዕድል ያገኙት ዐፄዎቹ በሀያ ሁለት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ፋሲል ከነማዎች ከዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪዎቻቸው ቅዱስ ጊዮርጊስና መቻል ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ወደ ሊጉ አናት የሚጠጉበት ወርቃማ ዕድል ቢያባክኑም በመጨረሻው ሳምንት ሻሸመኔ ከተማን አሸንፈው ወደ ድል ተመልሰዋል። በነገው ዕለትም ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ ተከታታይ ድል ካስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ዐፄዎቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ  ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አላቸው። በነገው ዕለትም በውድድር ዓመቱ አስራ ስድስት ግቦች ያስቆጠረና በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስመዘገበው የአዳማ ከተማ የፊት መስመር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

በአዳማ ከተማ በኩል ከክፍያ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ምክንያት ባለፈው ጨዋታ ካልነበሩት ሰባት ተጫዋቾች ውስጥ ቻርልስ ሪባኑ ዳግም ከስብስቡ ጋር የተቀላቀለ ሲሆን በተለያዩ ጥያቄዎች እየታመሰ የተሟላ ልምምድ ለመሥራት ተቸግሮ ከቆየው ስብስብ ውስጥ አድናን ረሻድም በቤተሰብ ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ታውቋል። በዐፄዎቹ በኩልም አቤል እንዳለ እና ሱራፌል ዳኛቸው ልምምድ ላይ ባጋጠማቸው ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።

በሊጉ ባደረጓቸው አስራ ሦስት ግንኙነቶች ፋሲል ከነማዎች አምስቱን በመርታት የበላይነት ሲይዙ አዳማዎች በአንፃሩ አራት ጨዋታዎችን አሸንፈው የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ። አዳማዎች 9 አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ዳንኤል ይታገሱ በረዳትነት ሲራጅ ኑርበገን እና ወጋየሁ አየለ አራተኛ በመሆን ደግሞ ሔኖክ አበበ በጋራ ይመሩታል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ከሽንፈትና ከአቻ ውጤት መልስ ድል ለማድረግ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።

ከአምስት ሽንፈት አልባ ጉዞ በኋላ በፋሲል ከነማ የሁለት ለባዶ ሽንፈት የገጠማቸው ሻሸመኔ ከተማዎች በስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሻሸመኔዎች የቀደመው መከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወታቸው በተወሰነ መልኩ ሚዛናዊ ለማድረግ ጥረቶች አድርገዋል። በተለይም በቀጥተኛና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር በሞከሩበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ የተሻሻለ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።
በነገው ዕለት ግን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በጥሩ ብቃት ያሉትን ሀድያ ሆሳዕናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ገጥመው ምንም ግብ ያላስተናገዱትን ብርቱካናማዎቹ ስለሚገጥሙ የፊት መስመራቸውን ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።


የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች በመሰብሰብ በድምሩ አስራ አምስት ሰብስበው በ12ኛ ደረጃነት የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ደረጃቸውን ለማስጠበቅ አልያም ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ብርቱካናማዎቹ ከሁለት ጨዋታዎች በፊት በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደ ደካማ የተከላካይ ክፍል ነበራቸው። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ የሚታይ ጥሩ ለውጦች በማድረግ መረባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣት ችለዋል። ጨዋታዎቹ ጠንካራ የፊት መስመር ካላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስና በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙ ሀድያዎች መሆኑ ደግሞ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል። ከቡድኑ ጋር መልካም አጀማመር ያደረጉት ኮማንደር ሽመልስ አበበ ቡድናቸው በመጨረሻው ሳምንት ላይ የታየበት የግብ ዕድሎች የመፍጠር ውስንነት ክፍተት መፍታት የሚያስችል ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ድሬዳዋ ከተማዎች የተመስገን ደረሰ ፣ ያሲን ጀማልና አብዱልፈታህ መሐመድን ግልጋሎት አያገኙም። ሻሸመኔዎች በበኩላቸው የቻላቸው መንበሩን ግልጋሎት አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የእርስ በርስ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል።

ለጨዋታው ሃይማኖት አዳነ በመሐል ዳኝነት ፣ ሙሉነህ በዳዳ እና እሱባለው መብራቱ በረዳትነት መስፍን ዳኜ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።