በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ 1-1 ተለያይተዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ሲገናኙ አዳማዎች በ13ኛው ሳምንት ባህር ዳር ከተማን 2ለ1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በግል ጉዳይ ጨዋታው በሚያልፈው አድናን ረሻድ ምትክ ኤልያስ ለገሰን ሲተኩ ዐፄዎቹ በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት ሻሸመኔ ከተማን 2ለ0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ጉዳት ባጋጠመው ሱራፌል ዳኛቸው ምትክ አማኑኤል ገብረሚካኤልን ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።
09፡00 ላይ በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት አዳማዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የጠራ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ቦና ዓሊ እና መናፍ ዐወል የዓየር ላይ ኳስ ብልጫ ለመውሰድ የሞከሩበትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ በግራ እግሩ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ጨዋታው 8ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መስዑድ መሐመድ ከመሃል ሜዳ የሰነጠቀለትን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ቦና ዓሊ ግብ አድርጎታል።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት የተቸገሩት ፋሲሎች የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን 15ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ይሁን እንዳሻው በኤልያስ ማሞ የተመቻቸለትን ኳስ ከሳጥን ውጪ መትቶት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ሲያስወጣበት ያ ኳስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ሲሻማ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤልም በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ማድረግ ችሎ ግብ ጠባቂው በድጋሚ ይዞበታል።
መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ የዐፄዎቹ ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬ ከአዳማው አጥቂ ቦና ዓሊ ጋር ተጋጭቶ በደረሰበት ጉዳት ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሆስፒታል ለማምራት ሲገደድ ይድነቃቸው ኪዳኔ እሱን ተክቶ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ ገብቷል።
የአቻነት ግብ ፍለጋ በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ስድስት ደቂቃዎቸ ውስጥ ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ ኳሱ መሬት ሳይነካ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ከዕረፍት መልስ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ዐፄዎቹ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴው ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የተሻለውን የግብ ዕድል ግን 54ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማዎች ተፈጥሯል። ቦና ዓሊ በግሩም ክህሎት ምኞት ደበበን አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ኃይል የለሽ ሙከራ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ይዞታል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 63ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ያደረጉት ፋሲሎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ተደርጎባቸዋል። ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ መስመር የቀነሰለትን ኳስ ጠርዙ ላይ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤልያስ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ዐፄዎቹ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት ለመጫወት ሲሞክሩ አዳማዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲጥሩ ተስተውሏል። ሆኖም ዐፄዎቹ 84ኛው እና 86ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ዕድል አግኝተው አጥቂው ጌታነህ ከበደ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጨዋታው በሚችሉት አቅም አጥቅተው ለመጫወት መሞከራቸውን ሲገልጹ ቀድመው ግብ ማስተናገዳቸው እና የግብ ዕድሎችን አለመጠቀማቸውን በመናገር ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረስ ይችሉ እንደነበር እና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባውን ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ እንቅስቃሴ መልካም እንደነበር ጠቁመዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ጨዋታው ሳቢ እንዳልነበር እና የአቻውን ውጤትም ፈልገውት እንደነበር አበክረው በመግለጽ ተጫዋቾች ብዙ ልምምድ እየሠሩ እንዳልሆነ እና ይህ ነገርም አስቸጋሪ እና አሳሳቢ እንደሆነም ጠቁመዋል።