ዶሜኒካን ሪፓብሊክ ለምታዘጋጀው የ2024 ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በማጣርያው እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን በደርሶ መልስ ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ተቀላቅሏል።
በአበበ ቢቂላ ስቴድየም በተደረገ የመጀመርያ ዙር ጨዋታ ሦስት ለባዶ በማሸነፍ የተሻለ የማለፍ ተስፋ ሰንቆ ወደ ስፍራው ያቀናው ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ በፕሪቶርያው ሉካስ ሞሪፔ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ከመጀመርያው ጨዋታ የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ የቀረበ ሲሆን በጨዋታው ያለ ጎል አቻ መለያየቱን ተከትሎ ወደ ሦስተኛው ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ በ3ኛው ዙር ግንቦት ላይ ዲሞክራቲክ ኮንጎን በፎርፌ አሸንፋ ያለፈችው ኬንያን የምትገጥም ሲሆን ይህንን ዙር ካለፈች በመጨረሻው ዙር የጅቡቲ እና ቡሩንዲን አሸናፊ የምትገጥም ይሆናል። ይህንን ጨዋታ ማሸነፍም የአፍሪካ አህጉርን ወክለው በዶሚኒካን ሪፐብሊክ በሚዘጋጀው የ2024 የፊፋ የሴቶች የአለም ዋንጫ ከሚሳተፉ ሦስት ሀገራት አንዷ የመሆን እድል ይሰጣል።