መረጃዎች| 57ኛ የጨዋታ ቀን

የ14ኛ ሳምንት መገባደጃ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ከአስከፊው የሦስት ለባዶ ሽንፈት በማገገም የሊጉን መሪ ያሸነፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሀያ አራት ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ፈረሰኞቹ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠቡበት ዕድል ለመጠቀም ወደ ሜዳ እንደሚገቡ እሙን ነው። ከገጠማቸው ተከታታይ የአቻና የሽንፈት ውጤቶች ወጥተው ወደ ቀደመው ብቃታቸው ለመመለስ በጥረት የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም እንኳ በመሀል በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ቢገጥማቸውም ከወዲሁ ለዋንጫ የሚገመቱትን ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በአንድ ሳምንት ልዩነት ማሸነፋቸው አሁንም ለዋንጫ ከሚጠበቁት መሀል መሆናቸውን አስመስክረዋል። በነገው ጨዋታ ግን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ድል ከተቀዳጁትና በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙት ወላይታ ድቻዎች እንደመሆኑ ፈተናው ቀላል እንደማይሆንላቸው መገመት ይቻላል። ፈረሰኞቹ ወሳኙ አጥቂያቸው አቤል ያለው ወደ ግብፅ ከሸኙ በኋላ ባደረጉት ጨዋታ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችሉም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ግን የወሳኙን ተጫዋች የግብ ማስቆጠር ድርሻ በተዋፅዖ ሊተካ የሚችል አጨዋወት ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።


በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ከጣሉ በኋላ ሀምበሪቾን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ወላይታ ድቻዎች በሀያ አንድ ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በነገው ጨዋታ ድል ካደረጉ ብያንስ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል በእጃቸው ስላለም በተለየ አቀራረብ ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል። የጦና ንቦቹ ምንም እንኳ ተከታታይነት ያለው ወጥ ብቃት ማሳየት ባይችሉም እንደተጋጣምያቸው ሁሉ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል አላቸው። የማጥቃት ጥምረቱ ምንም እንኳ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ላይ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ባይችልም፤ በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ቀላል ግምት የማይሰጠው ጥምረት ነው። በተለይም በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው ወጣቱ ቢንያም ፍቅሩ በነገው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ወላይታ ድቻዎች ከፀጋዬ ብርሀኑ ውጭ በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

18 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ወላይታ ድቻ 5 ድሎችን አሳክተዋል። አራት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 25 ወላይታ ድቻ ደግሞ 14 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ጨዋታው በባህሩ ተካ ዋና ዳኝነት ይመራል፤ ረዳቶቹ ሆነው የተመደቡት ደግሞ ሙልነህ በዳዳ እና ደረጄ አማረ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ዳንኤል ይታገሱ ተሰይሟል።


ኢትዮጵያ መድን ከ ወልቂጤ ከተማ

ሁለት ድል የተራቡ ክለቦች የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

በተከታታይ ድል አልባ ጉዞ አድርገው በአስር ነጥቦች የወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች አሸንፈው ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካት በጥሩ አቋም የማይገኙት መድኖች የመጀመርያው ዙር ከመጠናቀቁ በፊት ያላቸውን የነጥብ ልዩነት አጥብበው ለመጨረስ በውጤት ደረጃ በአንፃራዊነት ከሚቀራረባቸው ቡድን ሦስት ነጥብ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ግቦች ያስተናገደው የመድን ተከላካይ መስመር በነገው ዕለት ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ የማጥቃት ክፍል ያለው ቡድን እንደመግጠሙ ይቸገራል ተብሎ ባይገመትም በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ግን ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ይገመታል። ወልቂጤ ከተማዎች ባለፉት ጨዋታዎች ኳሱን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ የአማካይ ክፍል ስለገነቡ መድኖች የአማካይ ክፍላቸው ላይ ለውጦች ማድረግ ይኖርባቸዋል።


ሁለት ተከታታይ ድል ካስመዘገቡ በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ አቻና አምስት ሽንፈት የገጠማቸው ወልቂጤ ከተማዎች በጥሩ ወቅታዊ አቋም አይገኙም። ሰራተኞቹ ከመጨረሻው የሊግ ድላቸው በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ጨዋታዎች አንዱ ነጥብ ብቻ ነው ያገኙት፤ ይህም የቡድኑ ወቅታዊ አቋም ማሳያ ነው። በበርካታ የሜዳ ውጭ ችግሮች ተወጥረው የሚገኙት አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን(8) ያስቆጠረ ቡድን አላቸው። አሰልጣኙ የተጠቀሰው የግብ ማስቆጠር ችግር መቅረፍና በጨዋታ በአማካይ 1.3 ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ላይ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሰራተኞቹ በቅርብ ጨዋታዎች ላይ በተሻለ መንገድ ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል፤ ሆኖም በአጨዋወቱ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ የማስቆጠሩ መነሻም ይህ ነው።

ኢትዮጵያ መድኖች ከቅጣትና ጉዳት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ወልቂጤዎች የወንድማገኝ ማዕረግ እና አሜ መሐመድ ግልጋሎት የማግኘታቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

በሊጉ ሁለት ጊዜ (ባለፈው የውድድር ዓመት) ተገናኝተው ቀዳሚውን መድን 2-1፣ ተከታዩን ወልቂጤ 2-0 አሸንፈዋል።

መለሰ ንጉሴ በዋና ዳኝነት ኤፍሬም ሀይለማርያም እና ዘመኑ ሲሳዬነው በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድቧል።