ዮናስ ማለደ ከሦስት የውድድር ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሊጋት ሃአል ሲመለስ የሊጉ ውዱ ተጫዋች የሆነው ሌላው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ላለፉት ሥስት የውድድር ዓመታት በጌንት እና መቼለን ሲጫወት የቆየው የ24 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች ከዓመታት የቤልጅየም ቆይታው በኋላ ወደ እስራኤል ተመልሶ ለማካቢ ቴል አቪቭ ፌርማውን አኑሯል።
በ2020/21 አሳዳጊ ክለቡ ማካቢ ናታንያን ለቆ ለቤልጅየሙ ጌንት ፊርማውን ያኖረው ይህ ተጫዋች ከክለቡ ጋር ሁለት የውድድር ዓመት ካሳለፈ በኋላ ለሌላው በቤልጅየም ዋናው ሊግ የሚሳተፈው መቼለን ፊርማውን ቢያኖርም ከክለቡ ጋር የነበረው ቆይታ ከአንድ የውድድር ዘመን በላይ መዝለቅ ሳይችል ቀርቶ ወደ እስራኤል በመመለስ በአየርላንዳዊው የቀድሞ የቶትንሃም፣ ሊቨርፑልና ኢንተርሚላን ተጫዋች ሮቢ ኪን ለሚሰለጥነው ማካቢ ቴል አቪቭ ፊርማውን አኑሮ በጨዋታዎች ላይም መሳተፍ ጀምሯል። ከዓመታት በኋላ ተመልሶ ባደረገው ጨዋታም በተጨማሪ ደቂቃ ቡድኑ አቻ እንዲለያይ ያስቻለች ግብ አስቆጥሯል።
ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ በሌላ ዜና ላለፉት ዓመታት በአሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከር ለሚሳተፈው ካንሳስ ሲቲ ሲጫወት ከቆየ በኋላ በጥር የዝውውር መስኮት የመጀመርያ ሳምንታት ላይ በሌላው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ መሳይ ደጉ ለሚሰለጥነው ማካቢ ሃይፋ ፊርማውን ያኖረው የ30 ዓመቱ ጋዲ ኪንዳ ወደ ክለቡ ከተዘዋወረ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። በወቅታዊው የትራንስፈር ማርኬት የተጫዋቾች ዋጋ መሰረት ውዱ የሊጋት ሃኣል ተጫዋች የሆነው ይህ በአዲስ አበባ ተወልዶ በአሽሆድ ያደገው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአንድ ወር የክለቡ ቆይታ አንድ ግብ አስቆጥሮ ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ በማቀበል ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።