የአንደኛ ዙር የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ነገ ጅማሮውን የሚያደርግባቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።
አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን
የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር በ11 ነጥቦች ልዮነት 6ኛ ላይ የሚገኙትን አዳማ ከተማዎችን 13ኛ ደረጃ ከሚገኙት ኢትዮጵያ መድን የሚያገናኝ ይሆናል።
ባልተፈታ የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ጉዳይ በሙሉ ስብስብ ልምምድ መስራት የናፈቃቸው አዳማ ከተማዎች ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እየተጋሉም ቢሆንም በ22 ነጥቦች በሰንጠረዡ 6ኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ።
ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች መነሻነት አስቸጋሪ አጋማሽን ያሳለፉት አዳማ ከተማዎች ከምንም በላይ የተሻለ ሁለተኛ ዙር ለማሳለፍ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮቻቸው መፍትሔ ማበጀት ይኖርባቸዋል።
ከዓምናው አስደናቂ የሊግ አፈፃፀማቸው ማግስት ፍፁም ደካማ የውድድር ዘመን ጉዞ እያደረጉ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች በሁለት ጨዋታ ብቻ ድል ሲያደርጉ በሰባቱ ሽንፈት አስተናገደው በተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ በመፈፀም በሰንጠረዡ በአስራ አንድ ነጥቦችን በመያዝ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ነገሮችን ወደ መስመር ለማስገባት አሁን ባላቸው የተጫዋች አማራጭ ስነልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ከመስራት በዘለለ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡት አሰልጣኝ ገብረመድህን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በተለይ የፊት መስመራቸው እና መሀል ክፍላቸው ላይ ለውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በአዳማ ከተማ በኩል ባለፉት ጨዋታዎች ከቡድኑ ጋር ካልነበሩት ተጫዋቾች በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ባለፈው ጨዋታ ያልነበረው አድናን ረሻድ ሲመለስ የተቀሩት ተጫዋቾች በነገውም ጨዋታ ግልጋሎት አይሰጡም ፤ በአንፃሩ በኢትዮጵያ መድን በኩል ሙሉ ስብስቡ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 20 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። መድን 3 ሲያሸንፍ የግንኙነታቸው እኩሌታ (10 ጨዋታ) በአቻ ውጤት ተጠናቋል። አዳማ 23 ሲያስቆጥር መድን 18 አስቆጥረዋል። በዚህ ግንኙነት አዳማ በመድን ሽንፈት ካስተናገደም 20 ዓመታት ተቆጥረዋል።
የቀትር 9 ሰዓቱን መርሃግብር በዋና ዳኝነት መስፍን ዳኜ ሲመሩት በረዳትነት ሙሉነህ በዳዳ እና እሱባለው መብራቱ አራተኛ ዳኛ በመሆን ደግሞ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ሆኖ ተመድቧል።
ሀምበሪቾ ከኢትዮጵያ ቡና
የምሽቱ መርሃግብር ሁለት በተፃራሪ መንገድ እየተጓዙ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኝ ይሆናል።
በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ሲታመሱ የቆዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ወደ መንበሩ ካመጡ ወዲህ ግን ነገሮች መልክ እየያዙ ያሉ ይመስላል ፤ አሁን ላይ በ25 ነጥቦች ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ ከመሪው መቻል ያላቸው የነጥብ ልዮነት ወደ 5 ዝቅ የማለቱም ጉዳይ ለደጋፊዎች ተስፋ የፈነጠቀ ይመስላል።
በአሰልጣኝ ነፃነት እየተመሩ በሊጉ ካደረጓቸው 7 ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያላስተናገዱት ቡናማዎቹ በ5 ጨዋታዎች ድል ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተለይ በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የሊጉ መሪ መቻል ላይ የተቀዳጁት የ4-0 ድል ለቡድኑ እድገት አይነተኛ ማሳያ ሲሆን ከዚህ ባለፈ በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በድምሩ 7 ግቦችን አስቆጥረው በተቃራኒው ምንም ያለማስተናገዳቸው እውነታ ለቡድኑ በነገው ጨዋታ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው የሚያስገድድ ነው።
ከ14 ጨዋታዎች በኃላ በ6 ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ሀምበሪቾዎች የመጀመርያው ዙር ፍፃሜን አጥብቀው የሚጠብቁ ይመስላሉ ፤ በግማሽ የውድድር ዘመን 10 ጨዋታዎችን የተሸነፈው ቡድኑ 21 ግቦችን አስተናግደው በአንፃሩ ያስቆጠሯቸው ግቦች መጠንም 6 መሆኑ የሊጉ ደካማው መከላከል እና ማጥቃት ባለቤትም እንዲሁ ያደርጋቸዋል።
ከቀናት በኃላ በሚከፈተው የአጋማሹ የዝውውር መስኮት እንደ ቡድን የጥራት ሆነ የአማራጮች እጥረት ያለባቸው ሀምበሪቾዎች በዚህ ረገድ ራሳቸውን ለመጠገን እንደሚጠቀሙበት ሲጠበቅ የነገው ጨዋታው ወደ እረፍት ከማምራታቸው በፊት የተሻለ የሞራል ስንቅ ይዘው ለመፈፀም ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ወንድማማቾቹ ዳግም እና ቴዎድሮስ በቀለ በሀምበሪቾ በኩል የነገው ጨዋታ ሲያመልጣቸው በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ የመስመር ተጫዋቹ ጫላ ተሺታ እንዲሁ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።
ሁለቱን ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚያገናኘውን የምሽቱን መርሃግብር በመሐል ዳኝነት ሀይማኖት አዳነ ፣ ረዳቶቹ በመሆን ደግሞ ኤፍሬም ሀይለማርያም እና ሚፍታህ ሁሴን አራተኛ ሆኖ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በመሆን ተሰይመዋል።