ጥሩ ፉክክር እና አራት ጎሎችን ያስመለከተን የአዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ 2ለ2 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።
በሊጉ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር 1ለ1 ከተለያየበት ጨዋታ ኤልያስ ለገሠን በቻርለስ ሪቫኑ በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሲሆን ከወልቂጤ ጋር ያለ ጎል አጠናቀው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው ዮናስ ገረመው እና ብሩክ ሙሉጌታን ፣ በአሚር ሙደሲር እና ያሬድ ዳርዛ ቦታ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።
የሳምንቱ የመክፈቻ መርሀግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የቀድሞው ተጫዋች ፣ ዳኛ እና በመጨረሻም የጨዋታ ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግል ለነበረው ይድነቃቸው ዘውገ (ቦቸራ) የህሊና ፀሎት ተደርጓል። ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በመሐል እና በመስመሮች በኩል እንደነበራቸው ብልጫ ደቂቃዎች ብዙም ሳይሻገሩ አከታትለው ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ ጎል አግኝተዋል። 4ኛው ደቂቃ በግራ የመድን የሜዳ ክፍል ከእጅ ውርወራ በተከላካይ ተጨርፋ የደረሰችውን ኳስ ቦና ዓሊ ደርሶት ሳያመነታ ወደ ጎል መቶ አቡበከር ኑራ ካወጣበት ከአንድ ደቂቃ መልስ አዳማ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። ከማዕዘን ምት መስዑድ ያስጀመራትን ኳስ ጀሚል ወደ ሳጥን አሻምቶ ፉዓድ በቶሎ አመቻችቶለት ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ግብ ሲልካት ቢኒያም አይተን በቀላሉ መረቡ ላይ አስቀምጧታል።
በአንድ ሁለት ቅብብል መሐል ሜዳው ላይ ከሚፈጠሩ ስብጥሮች በኋላ ከመስመር የሚነሱ ፈጣን ተጫዋቾቻቸው እገዛ በመጠቀም በጥልቀት የሚጫወቱት አዳማዎች ሀያ ደቂቃዎችን የበላይነትን በመያዝ በተደጋጋሚ የመድንን የግብ ክልል ደርሰው ሲረብሹ ተስተውሏል። 8ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ታረቀኝ ሳይጠበቅ ከርቀት አክርሮ መቶ አቡበከር ኑራ ከመለሰበት ሙከራ በኋላ መድኖች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተወሰነ መልኩ ጥረት ያደረጉበትን ሂደት አይተናል። የሜዳውን የቀኝ ክፍል የአብዱልከሪም እና አቡበከርን ጥምረት በመጠቀም ያሬድ ዳርዛን ዋነኛ የጥቃት ምንጫቸው ለማድረግ የሚታትሩት መድኖች የአዳማ የግብ ክልል ደርሰው ግልፅ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ በመቸገራቸው ከርቀት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሁለት ሙከራዎችን በወገኔ ገዛኸኝ አማካኝነት ለማድረግ ተገደዋል።
ፈጠን ባሉ እንቅስቃሴዎች ጨዋታውን ቢጀምሩም ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በተጋጣሚያቸው መድን በተለይ የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ለመበለጥ የተገደዱት አዳማ ከተማዎች ጠንካራ ሙከራዎችን አያስተናግዱ እንጂ በኳስ ቁጥጥሩ የኋላ ኋላ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። እንደነበራቸው መልካም እንቅስቃሴ ግልፅ የግብ ዕድሎችን የማድረግ ውስንነት የነበረባቸው መድኖች 40ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ከቀኝ በጥሩ እይታ የሰጠውን ወገኔ ከጀርባው ነፃ ለነበረው አቡበከር ወንድሙ አመቻችቶለት ተጫዋቹም ወደ ጎል ሞክሮት ሰይድ ሀብታሙ በአንድ ለአንድ ግንኙነት አድኖበት ጨዋታው በአዳማ የ1ለ0 መሪነት ተጋምሷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ቡድኖቹ የአንድ ተጫዋች ቅያሪን በተመሳሳይ አድርገዋል። አዳማ ፉዓድ ኢብራሂምን በአድናን ረሻድ ፣ መድኖች አቡበከር ወንድሙን በብሩክ ሙሉጌታ ለውጠዋል። መድኖች ብሩክን ለውጠው ካስገቡ በኋላ ከአጋማሹ መጀመር አንስቶ የተሻሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ችለዋል። 48ኛው ደቂቃ ከወገኔ እግር ስር ያሬድ ዳርዛ ያገኘውን ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት አክርሮ መቶ ሰይድ ሀብታሙ በጥሩ ቅልጥፍና ያደረጉትን ፈጣን ሙከራ መክቶባቸዋል። መድኖች ኳስን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በተረጋጋ መልኩ ብልጫውን ወስደው ሲደርሱ ቢስተዋልም የፊት አጥቂዎቹ መሐመድ እና ያሬድ እግራቸው ስር የሚደርሱ ኳሶችን መጠቀም አለመቻላቸው የኋላ ኋላ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ሽግግር በሚጫወቱበት ወቅት ቀላል የማይባሉ አደገኛ ዕድሎችን በተቃራኒው በአዳማ አስተናግደዋል።
58ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች በዚህ የጨዋታ መንገድ ከቀኝ ሜዳ ዮሴፍ ሰብሮ ገብቶ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ወደ ውጪ ከወጣች በኋላ ጫናቸውን በሂደት ማሳደር የቀጠሉት አዳማዎች ተጨማሪ ጎልን አክለዋል። 68ኛው ደቂቃ ከአዳማ የኋላ ክፍል በረጅሙ የተጣለን ኳስ የመድኑ ተከላካይ ያሬድ ካሳዬ በቢኒያም ጫና ውስጥ ገብቶ ጨረፍ አድርጎ ለግብ ጠባቂው አቡበከር የሰጠውን ኳስ አቡበከር መቆጣጠር ተስኖት የሾለከችበትን ኳስ ቢኒያም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ቶሎ ቶሎ በሽግግር መጫወትን የጀመሩት መድኖች ብዙም ሳይቆዩ ወደ ጨዋታ የምትመልሳቸውን ግብ 70ኛው ደቂቃ ከመረብ አገናኝተዋል።
ያሬድ ከቀኝ ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ ንጋቱ በቀጥታ መቶ ሰይድ ሲተፋው ብሩክ ጎል አድርጎታል። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች እየጣለ ባለው ዝናብ ውስጥ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ መድኖች በድግግሞሽ በፈጠሩት ጫና የአቻነት ጎልን ማግኘት ችለዋል። 82ኛው ደቂቃ ወገኔ ከቀኝ እየገፋ ገብቶ ያሻገራት እና በአዳማ ተከላካዮች ተነካክታ ያሬድ ዳርዛ ከሁለት ሙከራዎች ተደርባ ያገኛትን ኳስ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ 2ለ2 ተሸጋግሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 90ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማዎች በመድን የግብ ክልል አካባቢ የቅጣት ምት አግኝተው ዮሴፍ አክርሮ ቢመታውም አቡበከር ኑራ በድንቅ ብቃት ካዳነ በኋላ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተቋጭቷል።