የ15ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ላይ የሚካሄዱ ሁለት መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ
በሀያ ሁለት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ወላይታ ድቻዎች በቅርብ ሳምንታት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ወጥ የሆነ ብቃት ማሳየት ባይችሉም በትልልቅ ጨዋታዎች ያላቸው ጥሩ ክብረወሰን በዚ ጨዋታ ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ያደርጋል፤ የጦና ንቦቹ በሊጉ አናት የተቀመጡትን ንግድ ባንክና ፋሲል ከነማ አሸንፈው ከቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና አቻ መለያየት ችለዋል። ይህም ቡድኑ በተጠባቂ መርሀ ግብሮች ያለውን ጥሩ ክብረወሰን ማሳያ ነው። የጦና ንቦቹ እንደከዚ ቀደም በጨዋታዎች በኳስ ቁጥጥር የላቀ ብልጫ መውሰድ ባይችሉም ጥቂት በማይባሉ መመዘኛዎች መሻሻል አሳይተዋል። ከነዚ ውስጥ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት አንዱ ነው፤ ቡድኑ በሲዳማ ቡና ከገጠመው የአራት ለአንድ ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተማ ከተቆጠሩበት ሁለት ግቦች ውጭ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ አላስተናገደም፤ ከዚ በተጨማሪ ወደ ግብነት ባይቀየሩም የቡድኑ የግብ ዕድሎች ፈጠራ አቅም ጥሩ መሻሻል አሳይቷል። በነገው ጨዋታም ቡድኑ ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ችግሩ ፈትቶ መቅረብ ይጠበቅበታል።
በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ከሳምንታት በኋላ ነጥብ ለማግኘት ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ። ባህርዳር ከተማዎች ድል ካደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል። ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ሁለት ለአንድ ካሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት አቻና አራት ተከታታይ ሽንፈት አስመዝግቧል፤ በስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ማሳካቱም ቡድኑ በመጥፎ ወቅታዊ አቋም እንዳለ ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም የመጀመርያውን ዙር በመጥፎ ተከታታይ ውጤቶች ላለማገባደድ በርካታ ማሻሻያዎች አድርጎ መግባት ይጠበቅበታል። ከሚጠበቁት ለውጦች አንዱ እጅግ የተዳከመው የፊት መስመሩ ነው፤ በተጠቀሱት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በነገው ዕለት በጊዜ ሂደት ጥሩ የመከላከል ብቃት የተላበሰው ቡድን እንደመግጠሙ ተሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል። ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ለውጦችን ይሻል።
በወላይታ ድቻ በኩል እንደ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ ፀጋዬ ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ብቸኛ ተጫዋች ሆኗል። በጣና ሞገዶቹ በኩል አጥቂው ሱሌይማን ትራኦሬ አሁንም ጉዳት ላይ ያለ ተጫዋች ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ስምንት ጊዜ ተገናኝተው (የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን አይጨምርም) ባህር ዳር 2፣ ድቻ አንድ ጊዜ አሸንፈው 5 ግንኙነታቸው አቻ ተጠናቋል። የጣና ሞገዶቹ 6፣ የጦና ንቦቹ 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ይህንን ጨዋታ በቢንያም ወርቃገኘሁ መሀል ዳኝነት ይመራል፤ ዘመኑ ሲሳይነውና ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ በረዳትነት ተመድበዋል፤ ሔኖክ አበበ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።
ሻሸመኔ ከተማ ከ መቻል
በዘጠኝ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሻሸመኔ ከተማዎች ነጥባቸውን አሻሽለው የመጀመርያውን ዙር ለማገባደድ የሊጉን መሪ ይገጥማሉ። ሻሸመኔዎች በቅርብ ሳምንታት የሚታይ መሻሻል ካሳዩ የሊጉ ቡድኖች ይጠቀሳሉ። ቡድኑ ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች አምስት አቻና አንድ ድል ቢያስመዘግብም በተጠቀሱት ሳምንታት አንድ ሽንፈት ብቻ ማስተናገዱ የመሻሻሉ ማሳያ ነው። ቡድኑ በአመዛኙ መከላከል ላይ ባመዘነ አጨዋወት ተንተርሶ በረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ቢያደርግም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ያለው ውጤታማነት በጥሩነት አይነሳም። በነገው ዕለትም ከሽንፈት ለማገገምና መሪነቱን ለማስጠበቅ በከፍተኛ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀውን የሊጉን መሪ እንደመግጠማቸው በብዙ ረገድ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
በሰላሣ ነጥቦች ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት መቻሎች መሪነታቸውን አስጠብቀው ዙሩን ለማጠናቀቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ። መቻሎች በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰባቸው የአራት ለባዶ ሽንፈት በፊት በተከታታይ አስራ አንድ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አልቀመሱም፤ በተጠቀሱት ሳምንታት ማግኘት ከሚገባው ሰላሳ ሦስት ነጥብ ሀያ ሰባቱን ማሳካታቸውም ቡድኑ ምን ያህል ውጤታማ ጉዞ እንዳደረገ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። በነገው ዕለትም ከአስከፊው ሽንፈት አገግመው በማሸነፍ መሪነታቸውን አስጠብቀው የመጀመርያውን ዙር ለማጠናቀቅ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከሚታትረው ሻሸመኔ ከተማ የሚገጥማቸውን ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻው የሊጉ መርሀ ግብር ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻለው የቡድኑ የአማካይ ክፍል በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። ከተጋጣሚ አጨዋወት አንፃር የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም ጠጣሩ የሻሸመኔ የመከላከል አደረጃጀት አልፎ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ያለው ፈተና ግን ቀላል እንደማይሆንላቸው ለመገመት አያዳግትም።
በሻሸመኔ ከተማ በኩል ወጋየሁ ቡርቃ እና ጌታለም ማሙዬ በቅጣት፤ ቻላቸው መንበሩ ደግሞ በጉዳት በነገው ጨዋታ አይኖሩም። በመቻል በኩል ምንይሉ ወንድሙ እና በኃይሉ ግርማ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው መቻል ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ አንዱን ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
መለሰ ንጉሴ በመሐል ዳኝነት፤ ወጋየው አየለና ደረጄ አመርጋ ደግሞ በረዳትነት ሲመደቡ ዳንኤል ይታገሱ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ሆኗል።