ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ኢትዮጵያ ቡና : ታክቲካዊ ትንታኔ

የኢትዮጵያ ኘሪሚየር-ሊግ 6ኛ ሳምንት
ህዳር 28/2007 ዓ.ም – 10፡30 ሰዓት (አዲስ አበባ ስታዲየም)
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ኢትዮጵያ ቡና
ታክቲካዊ ትንታኔ – በሚልኪያስ አበራ

 


ሁሌም የስታዲየማችን ደባብ እንዲህ እንዲያምር በሚያስመኘን የሁለቱ ከተማችን ታላላቅ የደጋፊ ባለሀብት ክለቦች መካከል ለ31ኛ ጊዜ የተደረገው የሸገር ደርቢ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በመጀመሪያው የጨዋታው ክፍለ-ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች 4-2-3-1 የተጨዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን ለመተግበር ሞክረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ፎርሜሽኑ ቡድን በመከላከል ቅርጽ ላይ ያሳድር ከነበረው structure አንፃር የታየ ነው፡፡ ምክንያቱም 4—4-2 የመምሰል ባህሪም ነበረው፡፡ ከሁለቱ አጥቆዎች በተለይም ፍፁም ገ/ማሪያም የጨዋታ position አኳያ ጊዮርጊስ 4-4-2 የሚጫወት አስመስሎት አምሽቷል፡፡ ነገር ግን ተጫዋቹ በተጋጣሚ የቀኝ ፍልባክና ከጐኑ ባለው የመስመር ተከላካይ መካከል (through the channels) የሚጫወት በመሆኑ እንደ መነሻ 4-2-3-1 የፈረሰኞቹ ፎሜሽን ነበር፡፡
ቡናዎቹ ደግሞ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ሜዳ አርባምንጭን 3 ለ 1 ካሸነፈው ቡድናቸው መስኡድን በቡድኑ አምበልና ተወዳጅ ተጫዋቻቸው ዳዊት እስጢፋኖስ ተክተው 4-3-3ን ተጠቅመዋል፡፡ (በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ከአማካይ ተከላካዩ ጋቶች ፓኖም በግራ (ዳዊት) እና በቀኝ (ኤልያስ) ሚና አንፃር ቡናዎችም በ 4-5-1 የሚጫወቱ መስለው አምሽተዋል፡፡
ምስል (1)

Bunna 1-0 Giorgis (1)

የቅዱስ ጊዮርጊስ የግራ መስመር
በትናንትናው ምሽት ጨዋታ ይህ መስመር የጊዮርጊስ ደካማው ክፍል ነበር፡፡ በጨዋታው በመጠኑ ከዘካርያስ ቱጁ (የግራ መስመር ተከላካይ) በቀር በእውነተኛ (ተፈጥሮዊ) የግራ መስመር አማካይነት ቦታውን ሲጠቀም የነበረ የጊዮርጊስ ተጨዋች አላስተዋልንም፡፡ ቡናዎች ደግሞ ጠንካራው የመስመር ክፍላቸው ይኼኛው እንደሆነ በተደጋጋሚ ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት ለመታዘብ ችለናል፡፡ ዴቪድ በሻህ (የቡና የቀኝ መስመር ተከላካይ) ሁለቱንም የጨዋታ phases (ማጥቃትንም መከላከልንም) ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚተገብር ፉልባክ ነው፡፡ ጊዮርጊሶች በዘከርያስና በቦታው የፊተኛው መስመር ካለው ፍፁም ውጪ ይህን ቦታ ሲጠቀም ነበረ ተጫዋች አለመኖሩ በመጀመሪያው አጋማሽ ዴቪድ የበለጠ በነፃነት ወደፊት ተጠግቶ Overlap እንዲያደርግ አግዞታል፡፡ በመጠቀም ዘካሪያስ ቱጂን በቦታው ሲያግዘው ያየነው ጥሩም ሲንቀሳቀስ ያልተመለከትነው ፋሲካ አሰፋው ነበር፡፡ ቡናዎች ይህንን ክፍተት በኤልያስ ማሞ ፣ አስቻለው ግርማና ዴቪድ በሻህ ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ የመስመሩን የጊዮርጊስ ብቸኛ ተጨዋች ዘካሪያስም Overload ሲያደርጉ ነበር፡፡ የጊዮርጊሶች ችግር ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ በጨዋታው ሁለቱን የፊት መስመር ተጫዋቾች ፍፁም ገ/ማሪያም እና ዳዋ ኢቲሳን ከአማካይ ክፍሉ ጋር የማገናኘት ሚናን እንዲወጣ ( link ለማድረግ ) የገባው አዳነ ግርማ ሌላው የቡድኑ ችግር ነበር፡፡ አዳነ ቦታውን ተብቆ የመጫወት ታክቲካዊ ስህተት ሲፈፅም ነበር፡፡ ከየትኛውም የሜዳ ክፍል ኳስን ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት እና እንቅስቃሴ በቦታው ላይ ክፍተትን ሲፈጥር ታይቷል፡፡ ይህም ጋቶች በነፃነት ወደ ፊት ሃይልና ፍጥነትን የቀላቀለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ አግዞታል፡፡ አዳነ በተለያዩ ግዚያት የተለያዩ ሚናዎችን ከመውስዱ አንፃር ቦታን ጠብቆ የመጫወት (positional play) ብቃቱ ለመውረዱ ምክንያት ይመስለኛል፡፡

የቡናዎች የመሃል ሜዳ የበላይነት
ቡናዎች በኘሪምየር ሊጉ ካሉ ክለቦች በቴክኒክም ሆነ በታክቲክ ግንዛቤ የተሻሉ የሚባሉ የመሃል ሜዳ አማካዮች ባለቤት ናቸው፡፡ ቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጐንም ይህኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጋቶች የመሃለኛው ሜዳ ትሪያንግል (ጐነ ሶስት) በተከከላካይ አማካይነት ለተከላካዮች ጥሩ ሽፋን ከመስጠቱም በላይ ቡድኑ ሲያጠቃም ጉልበትን የቀላቀለ ተጭኖ መጫወት (Aggressive pressing) ድርሻም ነበረው፡፡
በእርግጥ ከፊቱ አዳነ በተደጋጋሚ ቦታው አለመገኘቱ የራሱ የሆነ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ኤልያስና ዳዊትም ከጋቶች በግራና በቀኝ የሚገኘውን ቦታ በጥሩ ሁኔታ ለመጠቀም ምክረዋል፡፡ ኤልያስ ማሞ በተለይ ቡና የማትቃት phase ላይ ሲሆን ወደ መስመር በመውጣት፣ ወደ መሃለኛው የሜዳ ክፍል በመግባትና ቢንያም አስፋን በማገዝ (አጥቂውን እና አማካኝ ክፍሉን link በማድረግ) የተሻለ ተንቀሳቅሷል፡፡
ዳዊት ግን ትክክለኛው የሜዳ ሚናው ግልፅ አልነበርም፡፡ ከዚህም በፊት በመስዑዱ ላይ የምንመለከተው ኳስ ባለበት ቦታ ሁሉ የመንቀሳቀስ ባህሪ አይተንበታል፡፡ ይህ ደግሞ ተጨዋቾቹ ለድካም ከማጋለጡ በላይ ቡድኑ ላይ ክፍተት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ዳዊት ለማጥቃት ወደፊት ሲሄድ ጊዮርጊሶች በቱሳ አማካኝነት በጥሩ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱበት የነበረው የቀኝ መስመራቸው ላይ የበለጠ ክፍተት ሲያገኙ አስተውለናል፡፡ ይህም የቡናው የግራ መስመር አማካኝ ጥላሁን ወልዴ የበለጠ የመከላከል ሀላፊነትን እንዲሸከም ሲያስገድደው ነበር፡፡ የጊዮርጊስ አጥቂዎች የ wide forwards (የሜዳውን ወርድ (የጐኒዮሽ ቦታ) የሚጠቀሙ ተጫዋቾች) ከመሆናቸው አንፃር ዳዋ ሁቴሳ ወደ መስመር እየወጣ ከቱሳ ጋር አህመድ ረሺድ ላይ (የቡና የግራ መስመር ተከላካይ) ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩ ነበር፡፡ ይህ መስመር ቡና በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፅምበት የምናየው ነው ፤ ጥላሁን መከላከሉ ላይ ተሳትፎ ቢኖረውም የበለጠ ወደ መሃል እየገባ መጫወት ባህሪ ስላለው በተደጋጋሚ አህመድ በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጫና ውስጥ ይወድቃል፡፡ ስለዚህም እንደ ዳዊት ያሉት የቡድኑ አማካዮች ( ከግራው መስመር ከመሰለፍ አንፃር) አህመድን በመከላከሉ አጨዋወት ሊረዱት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ ቦታን ጠብቆ ከመጫወት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው ይመስለኛል፡፡ በቀኝ መስመር በ wide forwards ሚና አስቻለው ግርማ ፈጣን እና ሚዛናዊ እንቅስቃሴው በዚኛውም ጨዋታ የታየ ነበር፡፡ አስቻለው በ Geometnical movement ( በሜዳው የተለያዩ አቅጣጫዎችና ማዕዝናት) ጥሩ በመንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ ቡና ሲያጠቃ ቢንያምን በማገዝ ፣ ዴቪድ Overlap እንዲያደርግ ክፍተት በመተው እንዲሁም ከመስመር ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ቦታ በመጠቀም የተሻለ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ ኤሊያስ ፣ ዳዊትና አስቻለው ተደጋጋሚ የቦታ ለውጥ ማድረጋቸው ቡና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴው የተሻለ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

ምስል 2

Bunna 1-0 Giorgis (2)

ሁለተኛው አጋማሽ
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር አሰልጣኝ ኔይደር አዳነን አስወጥተው ኡስማን ኢምቤንጎን አስገቡ፡፡ ይህም ብራዚላዊው አሰልጣኝ የቡናዎችን የመሀል ክፍል ሜዳ የቁጥር የበላይነት ለማጥበብና የመስመር ሚዛንን ለመጠበቅ ያደረጉት ይመስላል፡፡ ኤምቤንጎ ቡናዎች የተሻለ ሲንቀሳቀሱበት የነበረው የቀኝ መስመር ላይ የዴቪድ በሻህ ሚናን በመገደብ እንዲሁም ፍጹም የበለጠ የማጥቃት ስራ ላይ እንዲያተኩር የሚያግዝ የግራ መስመር አማካኝ ነበር፡፡
በዚህ ሂደትም ኢምቤንጎ ወደ መሀል እየገባ የቡናን አማካዮች (ዳዊትንና ጋቶችን) press ለማድረግ መጠነኛ ሙከራ አድርገዋል፡ ጊዮርጊስም ወደ 4-4-2 የተጠጋ ፎርሜሽንን ተግብሯል፡፡
በ49ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ከኤሊያስ ማሞ ያገኛትን ኳስ የጊዮርጊስ የግራ መስመር ተከላካይ ዘካሪያስ ቱጂን ጀርባ በመጠቀም ቡድኑን መሪ አደረገ፡፡ አሰልጣኝ ዶሳንቶስ በ59ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ ጥሩ ያልነበረውን እና እጅግ ለተከላካዮች ቀርቦ ሲጫወት ያመሸው ፋሲካ አስፋውን ቀይረው በቀይ መስመር ተከላካይነት የሚታወቀውን አሉላ ግርማን ወደፊት የተጠጋ የአማካኝነት ሚና ሰጡት፡፡ ተስፋዬ አለባቸውም የተከላካይ አማካኝነት ሚና ከመጀመሪያው 45 የበለጠ እንዲወስድ በማድረግና አሉላን ወደፊት በማስጠጋት እንዲሁም ቱሳን በግራ ኢምቤንጎን በቀኝ በማቀያየር ቡና ላይ ተደጋጋሚ የማጥቃት ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ቅያሬው (የተጨዋቹም positioning) በጊዮርጊስ እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ዴቪድ በሻህ በቀኝ አህመድ ረሺድ በግራ ለመሐል ተከላካዮቹ (ሚሊዮንና ኤፍሬም) ቀርበው በመጫወታቸው ኢምቤንጎ እና ቱሳ በቢያድግልኝና ዘካሪያስ እየታገዙ (Overlapping movement) ክፍተቱን ለመጠቀም ጥረዋል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ ላይም ቱሳ (በሀይሉ አሰፋ) የፍጹም ቅጣት ምት ያስገኘው በዚሁ ሂደት ነበር (ፍጹም የተሰጠውን ፍ.ቅ.ምት ቢስተውም)፡፡ ፍጹም ቅጣት ምቱ የቡናን ተጫዋቾች ቁጥር ያስቀነሰም ነበር፡፡ (ጥፋቱን የሰራው ጥላሁን ወልዴ በቀይ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል)፡፡ ጊዮርጊሶች አሉላን ቀይረው ካስገባበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተስተዋው መስመሮቹም (ሁለቱንም) ሚዛናዊነት መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡ ይህም ቡድኑ ምንያህል በመጀመሪያው 45 የግራውን መስመር እንዳልተጠቀመበት አመልካች ነው፡፡
የቡናው አጥቂ ቢኒያም ወደኋላ እየተመለሰ የመሐል ክፍሉን ማገዙ ሌላኘው የቡና ጠንካራ ጎን ነው፡፡ አሰልጣኝ ዶሳንቶስ ጊዮርጊስ ሲያጠቃ ፋሲካ የቢኒያም እንቅስቃሴን እዲከታተል ትእዛዝ ማስተላለፋቸው (በምልክት) ቢኒያም ሁለገብነቱ ለተጋጣሚ ተከላካዮች አስቸጋሪ መሆኑን የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡ አሉላም በግራው መስመር እንዲሁ በቀኙ በስር ተከላካዮች አማካዮች መካከል እየገባ የመቀባበያ አማራጮችን (passing line options)፣ ወደፊት እየሄደም የጥቃት አቅጣጫዎችን (Attacking angles) ሲያሰፋ ተመልክተናል፡፡ የቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻም ቢኒያምን አስወጥተው ሚካኤል በየነን በተከላካይ አማካኝነት ሚና አስገቡ፡፡ ይህም የጊዮርጊስን ጫና ለመቋቋም የታለመ ነበር፡፡
ከቅያሪዎች በኋላ ጨዋታው በቡና አሸናፊነት እስኪጠናቀቅ ድረስም 4-4-1 ፎርሜሽን ኢትዮጵያ ቡና የተገበረው ፎርሜሽን ነበር፡፡
ምስል 3

Bunna 1-0 Giorgis (3)

 

ያጋሩ