በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የሁለተኛው ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ ሀዋሳ ከተማ በግብ ሲንበሸበሽ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል።
ረፋድ አራት ሰዓት ሲል በጀመረው የሁለተኛ ቀን በመጀመሪያ መርሃግብር ሀዋሳ ከተማን ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውን ሀዋሳ ከተማዎች በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈዋል።
በመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ መልክ በነበረው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በጥንቃቄ የተጫወቱበት ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች መካከል የግብ ሙከራዎች ቢኖሩም የሀዋሳ ከተማዎች ግን አንፃራዊ የበላይነት የታየበት ነበር።
ልደታዎች በአንፃሩ አልፎ አልፎ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመሄድ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት ቢያድርጉም አስፈሪ ሙከራዎችን ግን ለማድረግ ተቸግረው አስተውለናል። የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ የሰከንዶች ዕድሜ በቀሩበት ወቅት ቱሪስት ለማ በአንድ ሁለት ቅብብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝታ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችላለች።
ሀይቆቹ በሁለተኛ አጋማሽ ከፍፁም ጨዋታ በላይነት ጋር የተንቀሳቀሱበት ነበር ፤ በአንፃሩ ልደታ ክፍለ ከተማዎች ደግሞ ፍፁም ደካማ አጋማሽን ለማሳለፍ የተገደዱበት ነበር።
በ61ኛው ደቂቃ ረድኤት አስረሳኸኝ ከመሰመር በኩል የልደታን ተከላካዮች አታላ በማለፍ በግል ጥረቷ ሁለተኛውን ግብ ለቡድኗ ስታስገኝ እሙሽ ዳንኤል ደግሞ በ72 ደቂቃ ከረድኤት አስረሳኸኝ የተሻገረላትን ኳስ ከመረብ አገናኝታ የሀዋሳን መሪነት ወደ 3-0 አሳድጋለች።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀር ቱሪስት ለማ በአንድ ሁለት ቅብብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ስታዋሀድ ቱሪስት ለማ የማሳረጊያዋን ግብ በሰከንዶች ልዩነት በማስቆጠር ጨዋታው በሀይቆቹ የ5-0 የበላይነት ተጠናቋል።
8:00 ሰዓት ላይ ጅማሮውን ባደረገው ቀጣይ የዕለቱ መርሃግብር ቦሌ ክፍለ ከተማ ሀምበሪቾን በመርታት መሪነታቸውን አስቀጥለዋል።
በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች በታዩበት በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ አደገኛ ሙከራዎችን ያደረጉበት ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ የፈፀሙት አጋማሽ ነበር።
ቦሌዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው ለመቅረብ የተጫዋች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው እንዲቀርቡ አስችሏል። ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ብዙ ሲጥሩ የነበሩት ቦሌዎች ጥረታቸው በ57ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነችው ቤተልሔም ስለሺ ከመሃል ሜዳ አካባቢ አክሪራ ወደግብ የመታችው ኳስ ወደግብነት ተቀይሮ ቦሌዎችን መሪ አድርጋለች።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የኳስ ቁጥጥራቸውን ያሳደጉት ሀምበርቾዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጠንካራውን የቦሌን የተከላካይ መስመር አልፎ ግባቸውን መድፈር ተስኗቸው ጨዋታው በቦሌዎች የ1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በዚህም በጊዜያዊነት ተነጥቀው የነበሩትን የሊጉ መሪነትን ዳግም መረከብ ችለዋል።
የሳምንቱ ማሳረጊያ በነበረው መርሃግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠረች ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን መርታት ችለዋል።
ተመጣጣኝ እና ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካቾች ባስመለከተው በዚህ መርሃግብር ሁለቱም ቡደኖች በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር። በመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ በቁጥር በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች በተደረጉበት በዚህ ጨዋታ የሁለቱም ቡድኖች ግብ ጠባቂዎች የተሻለ ቀን ያሳለፉበት ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻለ አጋማሽ ያሳለፉ ሲሆን በዚህም ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአመዛኙ ለግብ ክልላቸው ቀርበው እንዲጫወቱ ማስገደድ የቻሉበት ነበር።ያለ ግብ ለመጠናቀቅ በተቃረበው ጨዋታ በተጨማሪ ደቂቃ ኤሌክትሪኮች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚ አንጋፋዋ ሽታዬ ሲሳይ ከመረብ በማዋሀድ ቡድኗን በስተመጨረሻም የወሳኝ ሶስት ነጥብ ባለቤት ማድረግ ችላለች።