በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 3ለ1 በሆነ ውጤት አዳማ ከተማን በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ሲገናኙ 9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ መድኖች በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች በተሻለ ግለት ጨዋታውን ቢጀምሩም አዳማዎች ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው መጫወት ችለዋል።
የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም 7ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ አማካኝነት ሲደረግ ዮሴፍ ታረቀኝ ከግራ መስመር በድንቅ ዕይታ የሰነጠቀለትን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ዐይተን ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ መልሶበታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ዮሴፍ እና ቢኒያም ባደረጉት ቅብብል የተፈጠረውን የግብ ዕድል ቢኒያም ሊጠቀምበት ሲል ተከላካዩ በርናንድ ኦቼንግ አግዶበታል።
ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት የተቸገሩት ኢትዮጵያ መድኖች 28ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው በግሩም ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ያገኘው ያሬድ ዳርዛ ያደረገውን ሙከራ የአዳማው የመሃል ተከላካይ ታየ ጋሻው አግዶበታል።
በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው የአጋማሹ የመጨረሻ 10 ደቂቃ መድኖች ብልጫውን በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። በተለይም 36ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አበራ ግብ ጠባቂው በቃሉ አዱኛ በስህተት ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ወርቃማ ዕድል ቢያገኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ራሱ መሐመድ አበራ ተጨማሪ ዕድል ቢያገኝም ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በቃሉ አቋርጦበታል።
ጨዋታውን ከጀመሩበት ቅጽበት በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እየተዳከሙ የሄዱት አዳማዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 45ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ያሬድ ዳርዛ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቃሉ አዱኛ መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ እጅግ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች 47ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ብሩክ ሙሉጌታ በግራው የሳጥኑ ጠርዝ ኳስ ይዞ ሲገባ ተስፋሁን ሲሳይ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አሚር ሙደሲር መረቡ ላይ አሳርፎታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ወገኔ ገዛኸኝ ከግራ መስመር በተሻገረለት ኳስ የግብ ጠባቂውን እጅ የጣሰ የጭንቅላት ኳስ ማስቆጠር ችሏል።
በፈጣን ሽግግሮች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት መድኖች 59ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ዕድል ፈጥረው ወገኔ ገዛኸኝ በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው መሐመድ አበራ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ ለጥቂት ሲወጣበት ከስድስት ደቂቃዎች በኃላ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ያሬድ ዳርዛ ግብ ጠባቂውን በቃሉ አዱኛን ለማለፍ ሲሞክር ጥፋት ተሠርቶበት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ግብ አድርጎታል።
በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን ሲፈጥሩ ተቀይሮ የገባው ነቢል ኑሪ ከዮሴፍ ታረቀኝ በተመቻቸለት ኳስ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ሲወጣበት 75ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤልያስ ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል።
ጥሩ ፉክክር በተደረገባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎችም አዳማዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ 86ኛው ደቂቃ ላይ ነቢል ኑሪ ከቢኒያም ዐይተን ጋር ተቀባብሎ ጥሩ የግብ ዕድል ቢፈጥርም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። በጭማሪ ደቂቃም የመድኑ አማካይ ንጋቱ ገብረሥላሴ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ መድን ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።