ዛሬ በተካሄደ አንድ ጨዋታ የጀመረው አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ነገ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ይቀጥላል፤ ኢትዮጵያ መድንን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚቀላቀል ቡድን የሚለየውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ
በ3ኛ ዙር አምስት አምስት ግቦች አስቆጥረው ተጋጣሚዎቻቸውን ያሸነፉት ሁለት ቡድኖች ነገ በሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ይገናኛሉ።
ደሴ ከተማን ሦስት ለአንድ አሸንፈው ውድድሩን የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በሦስተኛው ዙር ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለውን ሀድያ ሆሳዕና በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው ወደ ዙር እንደመብቃታቸው ትልቅ ግምት እንዲሰጣቸው ያደርጋል። በጨዋታው በዮናታን ኤልያስ፣ ዘላለም አባቴ፣ አብነት ደምሴና የቢንያም ፍቅሩ ሁለት ግቦች ታግዘው ሀድያ ሆሳዕናን ያሸነፉት የጦና ንቦች በሁለት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረ የፊት መስመር አላቸው። በተለይም በውድድሩ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስቆጠረውና ከቀናት በፊት ከነገው ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተካሄደ ጨዋታ ላይ የጦና ንቦች ነጥብ ተካፍለው እንዲወጡ ያስቻለች ወሳኝ ግብ ያስቆጠረው ወጣቱ አጥቂ ቢንያም ፍቅሬ በነገው ጨዋታ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
በሁለተኛ ዙር ሀምበሪቾን ሁለት ለአንድ በሦስተኛው ዙር ደግሞ ሻሸመኔ ከተማን አምስት ለሁለት በማሸነፍ ወደ አራተኛው ዙር የተሻገሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአፍሪካ ውድድሮች ያላቸውን ተከታታይ ተሳትፎ ለማስቀጠል ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ። በፕሪምየር ሊጉ ሀያ አምስት ግቦች ያስቆጠሩት ፈረሰኞቹ በኢትዮጵያ ዋንጫም በሁለት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች በማስቆጠር ጠንካራ የአጥቂ ክፍል እንዳላቸው አስመስክረዋል። ሆኖም በሁለቱም ውድድሮች አስር ግቦች ያስቆጠረላቸውን ወሳኝ የፊት መስመር ተሰላፊ አቤል ያለው ካጡ በኋላ ባካሄዷቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠራቸውን ሲታይ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ወደ ሌሎች የግብ ምንጮች እንዲያማትሩ ሊያስገድዳቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል።