የኢትዮጵያ ዋንጫ | አራቱ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ሙሉ ለሙሉ ተለይተዋል

በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ አርባምንጭ ከተማን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ 2ለ0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀሉን አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ አራተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተገናኝተዋል። መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ የኃይቆቹ ፈጣን አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን 5ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።


ጨዋታው 14ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጠሮበታል። ዓሊ ሱሌይማን ከተባረክ ሄፋሞ የተመቻቸለትን ኳስ አስደናቂ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ግብ ጠባቂውን በማለፍ መረቡ ላይ አሳርፎት ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችሏል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት የተቸገሩት አዞዎቹ 28ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን አድርገው እንዳልካቸው መስፍን ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም አህመድ ሁሴን ከግራ መስመር በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የላይ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ በተሻለ ግለት ጨዋታውን የጀመሩት አርባምንጮች ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ተገኝ ከረጅም ርቀት ሞክሮት በተከላካይ ተጨርፎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት በወጣው ኳስ የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን ቢጀምሩም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ባለበት ማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዋሳዎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሠራዊት ሰያ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው አቤኔዘር ዮሐንስም ሊጠቀምበት ሲል ግብ ጠባቂው በድጋሚ አምክኖበታል። ሆኖም ግን በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ራሱ አቤኔዘር ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ተጨማሪ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።


ጥሩ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ አዞዎቹ በቁጥር በመብዛት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ቢደርሱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ስኬታማ የነበሩት ኃይቆቹ 74ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ኢዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሠራዊት ሰያ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ተባረክ ሄፋሞ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ይህም የተሻለው ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሀዋሳ ከተማ ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለ አራተኛ ቡድን መሆን ሲችል በቀጣይም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚጫወት ይሆናል።