በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሰባተኛ ሳምንት ሶስተኛ ቀን ውሎ ሶሰት ጨዋታዎች ተደርገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከአዳማ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሶስት ግቦች አዳማ ከተማን አሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተቀዛቀዘ ጨዋታ ያስመለከቱን ሲሆን አዳማ ከተማ ሙሉ በሙሉ የመከላከል ባሕርይ ያሳዩበትን አርባ አምስት አሳልፈዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲገቡ ታይተዋል። የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አካባቢ ተቀይራ የገባችው ሽታዬ ሲሳይ ጨዋታውን መቀየር ብትችልም ግብ ሳይቆጠር ያለ ምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ኤሌክትሪኮች በ55ኛው ደቂቃ ምርቃት ፈለቀ በራሷ ጥረት ከርቀት መትታ ባስቆጠረችው ግብ 1ለ0 መምራት ሲችሉ በመነቃቃት እንዲጫወቱም አድርጋለች። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና በመፍጠር የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች በ70ኛው ደቂቃ ከመስመር አጠገብ ሽታዬ ሲሳይ ጨርሳ ያሻገረችውን ኳስ ምርቃት ፈለቀ በድጋሚ በማስቆጠር መሪነታቸውን አጠናክራለች።
አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ የኳስ ቁጥጥር በማድረግ ደካማ ሁለተኛ አርባ አምስት አሳልፈዋል። ድክመታቸውን የተረዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆም በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ሽታዬ ሲሳይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር ኤሌክትሪክ 3ለዐ እንዲያሸንፍ አድርጋለች።
ቀን 8 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተገናኝተው ንግድ ባንክ በሰፊ ግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል።
ጨዋታው ከመጀመሩ ፈታኝ የግብ ሙከራዎች በታዩበት በዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍፁም የጨዋታ በላይነት ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ በመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው የተገኙት ንግድ ባንኮች ከተደጋጋሚ ግብ ሙከራ በኋላ በ20ኛው ደቂቃ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ በሚገርም ሁኔታ ከርቀት መትታ ባስቆጠረችው ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃሩ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተቃራኒ ቡድን ሄዶ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም ግን አልፎ አልፎ የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች ሁነኛ አጥቂ በማጣታቸው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ተስተውሏል። በ38ኛው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ በመስመር በኩል በራሷ ጥረት ኳስን ይዛ በመግባት ኳስና መረብ አገናኝታ ንግድ ባንክ 2ለ0 እየመራ እረፍት እንዲወጣ አድርጋለች።
በሁለተኛው አጋማሽም ጥንካሬያቸውን ያስቀጠሉት ንግድ ባንኮች ምናልባትም በርከት ያለ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን የግብ ሙከራ አድርገዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጥር የተቃረበ ኳስ በእርስ በርስ ቅብብል ንግድ ባንኮች ይዘው በሚገቡበት ሰዓት የጊዮርጊስ ተከላካዮች በሠሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግንተዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱንም ሴናፍ ዋቁማ አስቆጥራ ልዩነታቸውን አስፍታለች።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሶስተኛ ግብ ተቆጥሮባቸው መረጋጋት ተስኗቸው በሠሩት ስህተት የተገኘውን ኳስ በ56ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ከመረብ ጋር አገናኝታ 4ለ0 እንዲመሩ አስችላለች። ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ሊገባደድ ሲቃረብ በ89ኛው ደቂቃ ሰርካለም ሳፊ ከሽንፈት ያልታደገቻቸውን ግብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጥራ ጨዋታው 4ለ1 እንዲጠናቀቅ አድርጋለች።
የሳምንቱ ማሳረጊያ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማን ከድሬዳዋ አገናኝቶ በሀዋሳ ከተማ የበላይነት ተገባዷል።
አስር ሰዓት ሲል በጀመረው ጨዋታ ግብ መቆጠር የጀመረው ገና በአራተኛው ደቂቃ ነበር። ሀዋሳ ከተማዎች ጨዋታው እንደጀመረ ነበር የግብ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት። በ4ኛው ደቂቃ እሙሽ ዳንኤል በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝታ ሀዋሳ ከተማ 1ለ0 እንዲመራ አድርጋለች።
ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በዚህም ጥረታቸው ሳይሳካ የመጀመሪያውን አጋማሽ 1ለ0 እየተመሩ ለመውጣት ተገደዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያለ የግብ ሙከራ አድርገዋል። በተለይም ድሬዳዋ ከተማዎች አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችን አግኝተው መጠቀም አልቻሉም። ሀዋሳ ከተማዎችም እንዲሁ ያለቀ ኳስ አግኝተው ሲያባክኑ ለመመልከት ተችሏል።
በ76ኛው ደቂቃ ቱሪስት ለማ ከመሃል ሜዳ አካባቢ የተጣለላትን ኳስ ወደ ግብ ክልል ይዛ በመግባት የድሬዳዋ ከተማን ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ አታልላ ግሩም ግብ አስቆጥራ ሀዋሳ ከተማ ልዩነቱን ሁለት እንዲያደርግ አስችላለች። በዚህም ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።