እድሳት በተደረገለት ድሬዳዋ ስታዲየም የሚካሄደው የሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ይጀምራል። የሁለተኛው ዙር መክፈቻ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
ባህርዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
ባህርዳር ከተማና ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች
ከስድስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ በቸርነት ጉግሳ ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ አሸንፈው የመጀመርያውን ዙር ያገባደዱት የጣና ሞገዶቹ በሀያ ሁለት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከሌሎች ክለቦች በተለየ በዝውውሩ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙትና ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ያስፈረመው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ትልቅ የግብ ማስቆጠር ችግር ታይቶበታል። አዳዲሶቹ ፈራሚዎችም በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ላስቆጠረው የማጥቃት ክፍል ያጠናክራሉ ተብሎ ይገመታል።
ሀምበሪቾን ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ልቀው
13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። መድኖች ከተከታታይ ሽንፈት ወጥተው በመጨረሻዎች ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ መለያየታቸውና በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ወደ ሩብ ፍፃሜው የሚያሻግራቸው ውጤት ማስመዝገባቸው በጥሩ የማሸነፍ ስነ-ልቦና እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል። ከዛ በተጨማሪ በውድድር ዓመቱ በሦስት ጨዋታዎች ብቻ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው የተከላካይ ክፍል ለማጠናከር ሚልዮን ሰለሞን ማስፈረማቸው ቡድኑን በብዙ ረገድ ያሻሽላል ተብሎ ይታመናል።
በባህርዳር ከተማዎች በኩል አጥቂው ሱሌይማን ትራኦሬ አሁንም ጉዳት ላይ ያለ ተጫዋች ነው። በኢትዮጵያ መድን በኩል ንጋቱ ገብረስላሴ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ ሲያመልጠው በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማሙት ሚሊዮን ሰለሞን እና አናንያ ጌታቸው የዝውውር ሂደታቸው ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሰ እና ኤልያስ መኮንን ረዳቶች ሔኖክ አክሊሉ በበኩሉ አራተኛ በመሆን ጨዋታውን ይመሩታል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀምበርቾ
በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ብርቱካናማዎቹ በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ሆነው የመጀመርያውን ዙር አገባደዋል።
ድሬዳዋ ከተማዎች የአሰልጣኝ ቅያሪ ካደረጉ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው የሚታይ መሻሻል ካሳዩ የቡድኑ ክፍሎች አንዱ ነው። ቡድኑ ከለውጡ በፊት በተካሄዱት የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ግቦች አስተናግዶ ነበር፤ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ግን ድንቅ መሻሻል አሳይቷል።
የመጀመርያውን ዙር በሰባት ነጥቦች የሰንጠረዡ ግርጌ ሆነው ያጠናቀቁት ሀምበሪቾዎች ከተከታታይ የአቻና የሽንፈት ውጤቶች ለመላቀቅ ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ። በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘውን ኢትዮጵያ ቡና በገጠሙበት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ጨምሮ በቅርብ ሳምንታት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ ወደ መከላከሉ ያዘነበለ ጠጣር አቀራረብ የነበራቸው ሀምበሪቾዎች በውጤት ረገድ መሻሻል ባያሳዩም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን መጠነኛ መሻሻል አሳይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማና ወላይታ ድቻን የመሳሰሉ በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኝ የፊት መስመር ያላቸውን ቡድኖች በገጠሙባቸው ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ማስተናገዳቸውም ቡድኑ ከቀደመው የመከላከል ድክመቱ አንፃር መሻሻል ማሳየቱ ማሳያዎች ናቸው።
ድሬዳዋ ከተማዎች ጉዳት ላይ ከሰነበቱት ተመስገን ደረሰ፣ አብዱልፈታህ ዓሊና ያሲን ጀማል በተጨማሪ ቀለል ያለ ጉዳት የገጠመው ዳዊት እስጢፋኖስ በነገው ጨዋታ አያሰልፉም። ከዛ በተጨማሪ ኤልያስ አህመድ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን እያሱ ለገሠ ከቅጣት መልስ በነገው ጨዋታ የሚሳተፍ ይሆናል። ክለቡ አሁንም በጊዜያዊ አሰልጣኙ ሽመልስ አበበ መሪነት ሲቀጥል በዝውውር መስኮቱም አንድ ተጫዋች እንደሚያስፈርም ይጠበቃል።
ሀምበሪቾዎች በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም። ሆኖም አቤል ከበደ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል። አዲስ አሰልጣኝ ፍለጋ ላይ ያለው ቡድኑ በቀጣዮቹ ቀናትም ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር ሊለያይ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው።
ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ ረዘም ካለ ዓመት በኋላ የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታዋን በረዳት ዳኝነት ከአብዱ አሊ ጋር በመሆን ስታገለግል አባይነህ ሙላት ለዚህ ጨዋታ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ይመራል።