ለጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሠ የህክምና ወጪ የተደረገውን የገቢ ማሰባሰቢያ ድጋፍ በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል። በገቢ ማሰባሰቢያው 2,244,312.00 ብር እንደተገኘ ይፋ ሆኗል።
በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ22 ዓመታት በላይ ያገለገለው ምስጋናው ታደሠ በአሁኑ ሰዓት በህመም ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በህትመት እና ኤሌክትሮኒክስ ብዙኀን መገናኛ ላይ ሲሠራ የቆየው ምስጋናው በነርቭ ዲስክ እና ተጓዳኝ በሆኑ ህመሞች መታመሙን ተከትሎ ለህክምና ከፍተኛ ወጪ ስላስፈለገው የድጋፍ ጥሪ የተደረገ ሲሆን በራሱ ጠቋሚነት በሦሰት የሙያ አጋሮቹ የተዋቀረ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የገንዘብ ማሰባሰብ እና የህክምና ሂደቱን የመከታተል ስራዎች ሲሰሩ ሰንብተዋል። በጋዜጠኛ ንዋይ ይመር፣ ኑራ ኢማም እና ሥዩም ፍቃዱ አማካኝነት የተዋቀረው ኮሚቴውም የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደቱን ለጊዜው ስላጠናቀቀ እና ከህክምናው ጋርም ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ለማስረዳት በዛሬው ዕለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ይህ ኮሚቴ ከተቋቋመ ጀምሮ ያለፉትን 20 ቀናት የገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ ሥራዎችን ሲሰሩ የነበረ ሲሆን ጎን ለጎንም የሙያ አጋራቸውን እንደ ቤተሰብ በማስታመም ከአጠገቡ በመሆን አጋርነታቸውን ሲያሳዩ እንደነበር ተገልጿል። ይህ ኮሚቴ ከመቋቋሙ በፊት ምስጋናው በራሱ ማኅበራዊ ገፅ የግል አካውንቱን ይፋ አድርጎ ከተደረገው ድጋፍ ውጪ ይህ ኮሚቴ ከ1.5 እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ ገንዘብ ለማሰባሰብ አልሞ ሲንቀሳቀስ ነበር። በዚህም የስፖርት ቤተሰቡ ዝቅተኛው ከ5 ብር ጀምሮ እስከ 100 ሺ ብር ድረስ በማዋጣት በአጠቃላይ 2,244,312.00 ብር እስከ ዛሬ ድረስ መሰብሰቡ ይፋ ሆኗል።
ይህ ገንዘብ ሲሰበሰብ 3/4ኛው የገቢ ማሰባሰቢያ ገንዘብ በአሸናፊ ዘለሌ የፌስቡክ ገፅ በተደረገ የቀጥታ የገቢ ማሰባሰቢያ የተገኘ ሲሆን ጋዜጠኛ ታምሩ አለሙም የላይቭ የገቢ ማሰባሰቢያ በግል ገፁ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ከፍ ያለ ገንዘብ እንዲገኝ ማስቻሉ ተገልጿል። የገቢ ማሰባሰቡን በበላይነት የመሩት ኮሚቴዎች ውጥናቸው እንዲሰምር ላበረከቱት ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ደግሞ የታምሩ አለሙ፣ አሸናፊ ዘለሌ፣ ሔኖክ ሄነሪ፣ ታምራት አበበ፣ አንዳርጋቸው ሰለሞን፣ ሸዋረጋ ደስታ፣ ይስሐቅ በላይ፣ ኤፍሬም ባህሪን እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ስም ጠቅሰው ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና ቸረዋል። አያይዘውም የስፖርት ቤተሰቡ ለሙያው እና ለሙያተኛው ያሳየውን ፍቅር አድንቀዋል።
ምስጋናው ከነርቭ እና ዲስክ ህመሙ ውጪም ሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች (ከኩላሊት እና ልብ ህመም ጋር የሚያሰጉ ምልክቶች) እንዳሉበት በህክምና ከተረጋገጠ በኋላ በመቅረዝ ሆስፒታል ያለፉትን 10 ቀናት ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ተጓዳኝ ህመሞቹ የቅርብ ቤተሰብ ክትትል ስለሚፈልጉ እና ወላጅ አባቱ እንዲሁም እናቱ በራሳቸው እንዲያስታምሙት ስለጠየቁ ከዶክተሮች ጋር ውይይት ተደርጎ ትናንት ከሆስፒታል ወጥቶ ዛሬ ወደ ትውልድ ሀገሩ ሀረር ከቤተሰቦቹ ጋር እንዳቀና ተገልጿል። ምስጋናው ወደ ሀረር ቢያቀናም ተጓዳኝ ህመሞቹ ሲሻሉት ከ2 ሳምንት በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ቼክ አፕ እንደሚያደርግ አልያም ሀረር ባለ ትልቅ ሆስፒታል ክትትሉን እንደሚቀጥል ተብራርቷል።
የተገለፀው 2,244,312.00 ብር ከስፖርት ቤተሰቡ ሲሰበሰብ በባንክ አካውንቱ 426 ትራንዛክሽን የነበረ ሲሆን በተለይ ኮሚቴው የተቋማትን በር እንዳያንኳኩ በላይቭ የነበረው የገቢ ማሰባሰቢ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ኮሚቴዎቹ አስረድተዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በውጪ ሀገር ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የድጋፍ ጥሪውን ተቀብለው ድጋፍ ላደረጉ በድጋሜ ምስጋና ቀርቦ የምስጋናውን የጤና ሁኔታ እና ቀጣይ ሂደቶች በተመለከተ በየጊዜው መረጃዎች ይፋ እንደሚሆኑ ተመላክቷል።
ሶከር ኢትዮጵያ ለጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሠ የህክምና ወጪ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያውን ላስተባበሩ ኮሚቴዎች ምስጋናውን እያቀረበ የሙያ አጋራችን ወደ ጤናው ተመልሶ ወደ ቀድሞ ሥራው እንዲመለስ መልካም ምኞቱን ይገልፃል።