ፕሪሚየር ሊግ ፡ መብራት ኃይል መሪነቱን ሲረከብ ቡና 4ኛ ተከታታይ ድል አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደው በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ለውጥ ያስከተሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በ9 ሰአት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናገደው መብራት ኃይል 2-1 አሸንፎ ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወደ ሊጉ አናት ተመልሷል፡፡ መብራት ኃይል በፒተር ንዋድካ ግብ ቀዳሚ ሲሆን በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው የተሸ ግዛው በ42ኛው ደቂቃ ዳሽንን አቻ አድርጎ የመጀመርያው ግማሽ ተጠኗቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የቀድሞው ታላቅ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ በ62ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ሲገባ ከተመልካቾች ሞቅ ያለ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን የመብራት ኃይል የአሸናፊነት ግብ ለማስቆጠርም የፈጀበት 5 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡

ውጤቱን ተከትሎ መብራት ኃይል ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የደረጃ ሰንጠረዡን በ12 ነጥቦች መምረት ጀምሯል፡፡

ከመብር ኃይል እና ዳሽን ጨዋታ በመቀጠል የተካሄደው የቡና እና ደደቢት ፍልሚያ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የቡና ቀዳሚ ግብ የተገኘችው በ39ኛው ደቂቃ በደደቢቱ ተከላካይ አዳሙ ሞሃመድ አማካኝነት ሲሆን ሁለተኛዋ ግብ ደግሞ በ67ኛው ደቂቃ በቢንያም አሰፋ አማካኝነት ተቆጥራለች፡፡

ቡና የመጀመርያዎቹን 2 ጨዋታዎች በሽንፈት ከጀመረ በኋላ ካለፉት 4 ተከታታይ ጨዋታዎች 12 ነጥቦች ሰብስቦ ከመብራት ኃይል ጋር በእኩል ነጥብ መምራት ጀመሯል፡፡

 

ሊጉ ነገ ሲቀጥል ቀሪ 5 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

ያጋሩ