የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-0 ሀምበርቾ

ይሄን ሦስት ነጥብ ለክቡር ከንቲባችን ማበርከት እንፈልጋለን።” አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ

“ብዙ ጨዋታዎች አሉ ከወዲሁ ተስፋ አንቆርጥም ረዥም ጊዜ አለን።” አሰልጣኝ መላኩ ከበደ

ብርቱካናማዎቹ በሜዳቸው ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሀምበርቾን 1ለ0 ከረቱ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው እንደታየው በጣም ጥሩ ነበር። አንደኛ የኳስ ብልጫ ወስደናል ሁለተኛም ውጤቱ ፤ ማሸነፋችን አይበዛብንም ጥሩ ነበርን።”

ዛሬ ያደረጋችሁት ለውጥ ምን ነበር…

“ብዙ የተለየ ነገር የለውም። ምናልባት የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ቲሞችን ዐይተህ የምትገባበት አልነበረም ምክንያቱም በሁለተኛ ማን ምን እንደቀየረ ስለማታውቅ በራሳችን መንገድ ነበር የገባነው። ሜዳችን እና ሕዝባችን ፊት እንደመሆኑ መጠን በኳስ ብልጫ በአሸናፊነት እንደምንወጣው እርግጠኞች ነበርን። ከእግዚአብሔር ጋር አሳክተነዋል።”

በሜዳችሁ የመጀመሪያ የሆነውን የዛሬ ጨዋታ ማሸነፋችሁ ምን ትርጉም አለው…?

“ትልቅ ትርጉም አለው። ምክንያቱም የሚታየው ደጋፊ አዳማ እያለን በተለያዩ ኤሌክትሮኒክሶች ነበር የሚከታተሉት እና አሁን ያንን በአካል መድገማችን ትልቅ ነገር ነው። የሞራል ስንቅ ነው የሚሆነን። ክቡር ከንቲባችንም በሜዳው ተገኝተው ጨዋታዎችን እየተከታተሉ ነበር እና በዚህ አጋጣሚ ይሄን ሦስት ነጥብ ለክቡር ከንቲባችን ማበርከት እንፈልጋለን።”

ስለ ሰው ሠራሹ ሜዳ…

“ሜዳው ምንም ነገር ይወጣለታል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም አንደኛ ላይሰንሱንም አግኝተናል ፤ ሁለተኛ ኳስ ለሚችል ቲም የተመቸ ነው። በኢትዮጵያ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ሜዳ ዐይተን አናውቅም።”

አሰልጣኝ መላኩ ከበደ – ሀምበርቾ

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው አሪፍ ነው ፤ የምጠብቀው ሦስት ነጥብ ነበር ግን የምንፈልገውን ነገር አላገኘንም። በብዙ ችግር ነው የመጣነው ያንን ችግር ደግሞ ቢያንስ በሦስት ነጥብ ለማከም ፈልገን ነበር ግን አልተሳካም። በቀጣይ እናሳካዋለን ብለን እናስባለን።”

ችግሩ ምንድነው…?

“ችግሩ ብዙ ነው። አንደኛ የወረቀት ችግር አለ ማለት የተጫዋቾች የተገቢነት ችግር አንዱ ይሄ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በጉዳት ምክንያት ያጣናቸው የሚጠቅሙን ተጫዋቾች አሉ። ብዙ ችግር አለ፤ ያንን ችግር ደግሞ ክለቡ ሊያስብበት ይገባል። የደሞዝ ክፍያ ነገር ማንም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው።”


ቡድኑ ራሱን አሻሽሎ በሊጉ ለመቆየት ስላለው ተስፋ…

“እንወርዳለን ብለን ተስፋ አናደርግም፤ ምክንያቱም ክለቡ ጋርም እኛ ጋርም ያሉት ነገሮች የሚስተካከሉ ከሆነና በጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾች ከተመለሱ ማሸነፍ  የምንችለውን ያህል እንጓዛለን። ብዙ ጨዋታዎች አሉ ከወዲሁ ተስፋ አንቆርጥም ረዥም ጊዜ አለን።

ስለ ዐዲሱ የመጫወቻ ሜዳ…

“ሜዳው ጥሩ ነው። የመጣነው አዲስ አካባቢ ነው፤ አዲስ ሜዳ ነው መጥፎ አይደለም እየለመድነው ስንመጣ ደግሞ የተሻለ ነገር ይፈጠራል። እንደ ሀገርም እንደ ከተማም የተሠራው ነገር ጥሩ ነው። ምስጋየም ከፍ ያለ ነው።”